እንቅልፍ ፈልጎኝ፤ ሊወስደኝ ሲመጣ፤
ነቅቼ ጠበቅኩት፤ ካልጋዬ ሳልወጣ፤
ተንጋልዬ ተኮስኩ፤ ሀሳቤን ወደ ላይ፤
ነጥሮ ደመሰሰኝ፤ ተጋጭቶ ከሰማይ።

ሌሊት እንቅልፍ አልወስድ ሲልህ፣ ወይ አንተም እንቅፉልን እምቢ ብለህ፣ ከአልጋው ተንጋለህ ጣራ ጣራውን ስታይ… ስንት ዘመን ይህን አድርግሃል? እስኪ ዛሬ ለለውጥ ብለህ ጣራውን ትተህ የተኛህበትን አልጋ አስበው፡፡
አልጋ ከእንቅልፍ፣ አልጋ ከብልግና፤ አልጋ ከውልደት፣ አልጋ ከህመም፣ አልጋ ከጭንቀት፣ አልጋ ከሞት፣ አልጋ ከሥልጣን፣ አልጋ ባልጋ ነው መንገዱ… ያዝ እንግዲህ!
አልጋ ላይ ተፈጥረህ፣ አልጋ ላይ ታልቃለህ፡፡ ብዙ ሰው የሚሞተው አልጋ ላይ ነው፡፡ ተጸንሰህ፣ ተወልደህ፣ ታመህ፣ አርጅተህ አልጋ ላይ ነህ፡፡ ከአልጋ ተነስተህ፣ ቆመህ መሄድ መራመድ እስክትችል ትኖር ትሮጥና ሲመሽ በስተርጅና ወደ አልጋህ ትመጣለህ፡፡
ሕይወትና ሞት፣ በአልጋ ነው፡፡ የምትወደውን ሰው እንኳ ወደ አልጋህ ታመጣዋለህ፡፡ ሁለት ሆናችሁ ወድቃችሁ፣ ሶስት ሆናችሁ ትነሳላችሁ፡፡ ሁለቱ ሲለዩህ፣ ብቻህን ትቀራለህ፡፡ አብረው የተኙት ወላጆችህ፣ አልጋ ላይ ፈጥረውህ፣ አልጋ ላይ ጥለውህ ከወዴት ሄደዋል? ምን ጨነቀህ! አንተም በተራህ ሌላውን ወደ አልጋ ታመጣለህ፡፡ አልጋ ባልጋ ባለጌ፣ አልጋ ባልጋ ባለጌ፣ አልጋ ባልጋ ባለጌ… ውልድ – ትውልድ፣ ውልድ!
ትውልድ ይቀጥላል፡፡ ትቀጥላለህ፡፡
አልጋ ላይ ተንጋለህ፣ ሕይወት በሐሳብ ያንጋልልሃል።
ሕይወት ማለት በወሲብ የሚተላለፍ በሽታ ይሆን? የሰው ልጅ ውስብስብነት መንስዔው መወሰብ መወሳሰብ፤ አንሶላ መጋፈፍ፤ መተቃቀፍ አልጋ ላይ አብቦ አልጋ ላይ መርገፍ…
ነገሥታት ኃይላቸውን የሚገልጹት በአልጋቸው ነው፡፡ በመካከለኛው ዘመን የአውሮፓ፣ ነገሥታት እንግዶቻቸውን የሚቀበሉት አልጋቸው ላይ ሆነው ነበር፡፡ የአገራችንም አልጋ፣ አልጋ ወራሽ ነበረው፡፡ አንተም ተራው ሰው፣ አልጋህን የምትዘረጋው ገመና ሁለመናህን ከምትደብቅበት መኝታ ቤትህ ነው፡፡ ሞት እስኪጎበኝህ አልጋህ የሕይወትህ ምስጢር ነው፡፡
ከአልጋ ውጭም እኮ ትሞታለህ፡፡ ወይ በመንገድ ትቀራለህ፤ ወይ ከጦር ሜዳ ትወድቃለህ፡፡ ያ ሲሆን አሟሟቴን አሳምረው ትላለህ፡፡ ሞቴ፣ እትብቴ የተወለደበት አልጋው ላይ ማለትህ ይሆን? ሆስፒታልም ቢሆን የሚጠብቅህ አልጋ ነው።
አልጋ ግን ሥልጣን ነውና ከሥልጣንህ ትወርዳለህ፡፡ ዞሮ መግቢያህ ከመሬት ይሆናል፡፡ አሟሟትህ አማረ አላማረ፣ ማለቂያህ «ኖረ፣ ነበረ፣ ተቀበረ» ነው፡፡ ፍጥረትህ አልጋ፣ መጥፋትህ ግን በመሬት ይሆን? ምናልባት አሟሟትህ አላምር ያለው አወላለድህ ጨዋነት ስለጎደለው ይሆን?
እንዲህ እያልክ ስታወጣ ስታወርድ፣ ያልጋው ላይ እንቅልፍ ያንሸራትተሃል፡፡ ዝም ያለ ሕልም፣ ከአልጋህ እንደተዘረጋህ፣ ለጥ እንዳልክ ፀጥ። ከዚያማ፣ በቃ ወይ ትነቃለህ ወይ አትነቃም፡፡
Subscribe to Ledesta
New writing in your inbox. English and Amharic.