
‹‹…መቶ አህዮች በአንድነት ቢያናፉ፣ ከአንድ ማሲንቆ የተሻለ ጣዕም ሊኖራቸው አይችልም።››
‹‹ከአድማስ ባሻገር››፣ ‹‹የህሊና ደወል››፣ ‹‹ሀዲስ››፣ ‹‹የቀይ ኮከብ ጥሪ››፣ ‹‹ደራሲው›› እና ‹‹ኦሮማይ»ን አነበብኳቸውና በዓሉን ላነጋግርህ አልኩት። ወዲያው ‹‹እሺ›› አለኝ። መቸም እንዴት ዓይነት ሰው መሰላችሁ! በዓሉ ያጫወተኝ ነገር ሁሉ በትክክል ይግባኝ አይግባኝ ባላውቅም፣ ብዙ ነገር አግኝቸበታለሁ። ላቀረብኳቸው ጥያቄዎች እንዲህ መልሶልኛል።
ጥያቄ። ደራሲ ለመሆን ምን ይጠይቃል?
‹‹ደራሲ ለመሆን ደምና ላብ ይጠይቃል›› ይላሉ። እያንዳንዱ ሰው በልቡ ውስጥ አንድ መጽሐፍ አለው። ግን ብዙዎቻችን አንጽፈውም። ይዘነው እንሞታለን።
ኦሮማይ፤ ገጽ 249
ጥያቄ። አንተሣ ጽፈኸው ሞትክ ወይስ ጽፈኸው ኖርክ?
መጻፍ አልቻልኩም። ሐቁ ይኽ አይደለም? ታዲያ ለምን ከራሴ እደብቀዋለሁ? መጻፍ አልቻኩም። በቃ የምለው አዲስ ነገር የለኝም። መባል ያለበት ሁሉ ከእኔ በተሻሉ ደራሲያን ተብሎ አልቋል። እና እንዲያው ነው ጊዜዬን በከንቱ የማጠፋው። የምለው ነገር የለኝም። ቢኖረኝም ምን እንደሆነ አላውቅም። ባውቀውም በቃላት ልገልጸው አልቻኩም። ቃላት…ቃላት መግለጽ ያለባቸውን አይገልጹም ያሾፋሉ።
ደራሲው፤ ገጽ 89
ጥያቄ። እኔ’ኮ የምጠይቅህ ጽፈኸው ሞትክ ወይስ ኖርክ ነው። ጽፈኸው እያየሁት መጻፍ አልቻልኩም ትለኛለህ? ይልቅ ንገረኝ፣ ወይስ መኖር መሞትህን ልትደብቀኝ ትሻለህ? አታምነኝም ልበል?
እኔ ኢትዮጵያውያንን አላምንም። ከራሴ ጀምሮ በጭምብል (በማስክ) ተሸፍነን የምኖር ሕዝቦች ነን። ለሰው የምናሳየው ገጽታና እውነተኛው ባሕርያችን የተለያዩ ናቸው። እንደ ተረታችን፣ ሥነ ጽሑፋችንና ንግግራችን ባሕርያችንም ሰምና ወርቅ ነው።
የቀይ ኮከብ ጥሪ፤ ገጽ 221
ጥያቄ። እንዴት ነው እምትናገረው? ይኽ ሁሉ መስዋዕትነትህ፣ ለማታምነው ሕዝብ ነበር ማለት ነው? ወይስ ‹‹ሰውን ውደደው እንጂ አትመነው›› እንዲባል፤ ባላምነውም እወደዋለሁ ለማለት ነው? ፈጽሞ አልገባኝም። ምናለበት ግልጽ ብትሆንልኝ?
ግልጽ መሆን ብሔራዊ ጠባያችን አይደለም። በልማዳችን ግልጽነት ከወራዳነትና ከእብደት ጋር የተያያዘ ጠባይ ነው።
የቀይ ኮከብ ጥሪ፤ ገጽ 92
ጥያቄ። ተው እንጂ! ይህን ያህል ውርጅብኝ እሚያስፈልገን አይመስለኝም። ይልቅ አዝነህብን ከሆነ ኀዘንህን ንገረና እንረዳህ?
እያንዳንዳችን ኀዘናችንን በጉያችን – ደስታችንን በጋራ። በዚህች አሳዛኝ ዓለም ላይ ኀዘን መጨመር ምን ያደርጋል? ሁሉም በልቡ በቂ ኅዘን የተሸከመ ስለሆነ፣ አንዱ ከሌላው የሚፈልገው ደስታን ብቻ ነው። መሆንም አለበት።
የቀይ ኮከብ ጥሪ፤ ገጽ 14
ጥያቄ። የፈለግኩት አጭር መልስ ነው። አዝነሃል ወይስ አላዘንኽም?
ደራሲ ኀዘን አይሰማውም፡ ስለ ሰው ልጅ ያዝናል። የራሱን ኀዘን ግን የለውም። እግዜር ሰውን በራሱ አምሳል ፈጠረ ይባላል። ግን ስለ ሰው ልጅ ያዝናል። ግን አይገርምም። ደራሲም እንደዚሁ ነው።
ኦሮማይ፤ ገጽ 361
ጥያቄ። መቸም መልስ አታጣም። ያም ሆነ ይህ ግን፣ ይህ ወርቅ ኅብረተሰብ የጣመህ አትመስልም። አንዳንድ ደራሲዎች ኅብረተሰቡ ሁሉ አይጥማችሁም ልበል?
ኅብረተሰቡም ሥራችን አይጥመውም። እኛ የኪነት ሰዎች ዕንቁ ነን እንላለን። የሚያየን የለም። ማር ነን እንላለን የሚልሰን የለም። የወለድናቸውን ልጆች አይስሙልንም። እንዲያውም ያንገላቱብናል።
የቀይ ኮከብ ጥሪ፤ ገጽ 82
ጥያቄ። የሚያንገላቱባችሁ ለምን ይመስልሃል? ‹‹የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ›› እንዲሉ፤ አንዳንዶቹ ስምና ገንዘብ ለመዝረፍ ሐቅን ያንቋታል። ሐቅ ደግሞ የሁሉም ጉሮሮ ነች። አንዱ ይውጥባታል። ሌላው ይዋጥባታል። የሆነ ሆነና ግማሹ ራሱን ለማነቅ፤ ግማሹ ደግሞ ሌላውን ለማነቅ በሚርመሰመስበት ኀብረተሰብ መኻል የኪነት ሰዎች ዓላማ ምን መሆን አለበት ትላለህ?
የኪነት ሰዎች ዓላማና ግብ ሐቅ ነው። ግን ስንት የኪነት ሰዎች ናቸው ለሐቅ ቆመው ለመሞት፣ ለመራብ፣ ለመታረዝና ለመጠማት የተዘጋጁት? ኅብረተሰቡ በንቀት ዓይን ቢመለከትንና ዋጋ ባይሰጠን አይገርመኝም። ሐቅን ያልጨበጠ ኪነት ዋጋም ሆነ ዘላቂነት የለውም። የታሪክ አተላና ዝቃጭ ሆኖ ይቀራል።
የቀይ ኮከብ ጥሪ፤ ገጽ 82
ጥያቄ። መጀመሪያ ‹‹ያንገላቱብናል›› አልክ፤ አሁን ደግሞ ‹‹ዋጋ ባይሰጠን አይገርመኝም›› ትላለህ። ብዙ ጊዜ እንደሱ ትጽፋለህ። በርግጥ ልክ ነህ ተቃራኒ ሐሳብን ወዲያና ወዲህ እያንቆሻበሉ አብሮ መንቆሻበል የሰዎች ባሕርይ ይመስላል። ግዴታም ነው ልትለው ትችላለህ፡፡ ግድ የለኝም። ግን አንዳንዴ በራስህ ሐሳብ መልሰህ የምትቀልድ ትመስላለህ። ተሳሳትኩ?
በራስ ላይ መቀለድ መቻል ጸጋ ነው። ጤናም ነው። ክፉ ዕድል ሆኖ፣ ብዙዎቻችን እንዲህ ዓይነቱን ጸጋ አልታደልንም።
ኦሮማይ፤ ገጽ 48
ጥያቄ። ግን ለምን እንደዚህ የተለየህ ሰው ትሆናለህ? ከዚህ ኅብረተሰብ የአንድ ሰው መለየት ስሕተት አይመስልህም?
ሺህ ሰዎች ተሳስተው፣ አንዱ ብቻ ልክ ሊሆን ይችላል። አዎን፣ መቶ አህዮች በአንድነት ቢያናፉ ከአንድ ማሲንቆ የተሻለ ጣዕም ሊኖራቸው አይችልም።
የህሊና ደወል፤ ገጽ 178
ጥያቄ። ቢሆንም ቢሆንም… አየህ ከኅብረተሰቡ ጋር ካልተስማማህ ወይ ይጨፈልቅኻል ወይ ይጠቀምብሃል። ይኸውልህ፣ ለምሳሌ አንተ ደራሲ ነህ። ከደራሲም እጅግ ደፋር ደራሲ። ‹‹እውነተኛ ከያኒ የሚኖርበትን ዘመን አየር ይተነፍሳል›› እንዲባል፤ ያለህበትን አየር እምትተነፍስ እውነተኛ ደራሲ ነህ። ግን ይኽ አደገኛ ነው። የሀገሬ ሰው እንደሚለው ‹‹የምኖርበት ሜዳ፣ የምገባበት ቀዳዳ የለም›› ነውና እንዳገኘህ መተንፈሱ ወደፊት ችግር ሊያመጣብህ ይችላል። ግን ለማን ብለህ? በዚያ ላይ ደግሞ በእኔ ግምት እውነተኛ ደራሲና ድሃ አንድ ይመስሉኛል። ‹‹ድሃን ምን ትሠራለህ እንጂ ምን ትበላለህ? የት ትኖራለህ?›› የሚል የለም። እና የኔ ጌታ አትቸገር። በችግርህ ጊዜ እሚደርስልህ የለም። አለ ቢባል እንኳ ቀን የተመቸ ለት ነው። ልክ እንደ ቴዎድሮስ። ቴዲ መቅደላ አፋፍ ላይ ቆሞ ሲጮህ- ያገር ያለህ እያለ ሲጣራ፣ ማን ደረሰለት? ደሩስበት እንጂ አልደረሱለትም። ግን ዛሬ ይኸው ታሪክ ሲቀሰቅሰን ደረስንለት። ፈጥኖ ደራሾች አይደለን!! ቢሆንም ይህ ለቴዲ ምንም አይጠቅመውም። እኔም ጽፈኸው ሞትክ ወይስ ጽፈኸው ኖርክ? ብዬ የምጠይቅህ ለዚሁ ነው። ያም ሆነ ይህ ሞትክም ኖርክም አንተ ምንም አትጠቀምም። እንዳልኩህ ነገ ቀን ሲመች፣ ሁሉም ስምህን እያንጠለጠሉ በላዩ ላይ ለመንጠልጠል ሲጣደፉ ታየዋለህ። ልክ አይደለሁ?
በዚህ ዓለም አንዱ የሌላው መሰላል ነው…እንደ’ኔ …እንዳንተ ያሉት ጧትና ማታ ህሊና! ህሊና! እያሉ በመጮኽ፤ ራሳቸውን የሚያታልሉት ግን፤ ርካብ ሆነው ነው የሚቀሩት። ጥንትም እንዲህ ነበር፣ አሁንም ተፈጥሮ ህጓን አልወጠችም።
ከአድማስ ባሻገር፤ ገጽ 36
ጥያቄ። ለካ ዝም ብለህ ነው የምታስለፈልፈኝ። ሆሆ! አንተን ማን ይችላል ልጄ! ሁሉን ነገር እያወቀ፣ ያወቀውን መልሶ የሚያደርግ ሰው ምንኛ የታደለ ነው። አንተም እንደዚያ ትሆን እንዴ? ሥራህ ሁሉ ይገርመኛል። በዚህ ሲሉህ፣ በዚያ ትመጣለህ። ለምሳሌ፣ አንዳንዴ እንዲህ መቅኖ ሊያጣ፣ ለዚህ አብዮት ጥብቅና የቆምክ ትመስለኝና ሌላ ጊዜ ደግሞ…?
በአብዮታዊ አስተሳሰብ አብዮታዊ ሕይወት መኖር እጅግ አስቸጋሪ ነው። ለፈተናው ተስገብግበው የሚቀርቡት ብዙዎች፣ ፈተናውን አልፈው የሚገኙት ደግሞ ጥቂቶች ናቸው። የደብተራ ጋጋታ፣ ቅዳሴውን አያሳምረውም።
የቀይ ኮከብ ጥሪ፤ ገጽ ……
ጥያቄ። ይኸዋ አላልኩህም። አንተ’ኮ እምትገርም ሰው ነህ። ግን እኔ ደግሞ መች እለቅህና፣ እንዲያውም አሁን ገና አገኘሁህ፣ ልብ አድርግ፣ እንግዲህ ከዚህ አነጋገርህ፣ ፈተናውን አልፎ መገኘቱ አስቸጋሪ ነው ብትልም ለውጡን ግን ትደግፋለህ። ታዲያ ይህ ከሆነ አንዳንድ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ላይ ለምን ትሳለቃለህ?
ግን ለውጥ ስለመጣ የግድ ዕድገት የሚከተል አይምሰልህ። የዕድገት ችግሩ ምርት አይደለማ። ችግሩ ሕዝቡ ያለው የማምረት ችሎታ ነው። የኋላ ቀርነት ትርጉም ምን ማለት እንደሆነ ይገባኻል? የኋላ ቀርነት ትርጉሙ በመሠረቱ የአእምሮ ኋላ ቀርነት ማለት ነው። እና ሶሻሊዝምን ስታመጣለት ሕዝቡ ምን የሚጋራ መሰለህ? እልም ያለ ድህነት። ሌላ ምን ሊጋራ ይችላል? ዝም ብላችሁ በምድረ በዳ ባትጮሁ አሁን ምናለበት? ባዶ ሕልማችሁን የቂል ገነታችሁን እዚያው ዩኒቨርስቲ ባዶ አየር ላይ ብትፈልጉ ካቡ። ሕዝቡን ግን ተውት።
ሀዲስ፤ ገጽ 107
ጥያቄ። አሃ! ለውጥ የሚባል ነገር ጨርሶ አያስፈልግም ማለትህ ነው?
ለውጥ ስለሆነ ብቻ በቀን ሦስት ሊትር ወተት የምትሰጠው ላም 25 ሊትር ልትታለብ አትችልም። ኢትዮጵያ የቸገራት ሠርቶ የሚያሳይ እጅ ነው።
የህሊና ደወል፤ ገጽ 178
‹‹ያሮጌው ትውልድ ሙጣጭ ፣ ያዲሱ የበኩር ልጅ፣ ያንዱ መጨረሻ፣ የሌላው መጀመሪያ መሆን እብደት ነው፤ ያሮጣል።››
ባለፈው ሣምንት ከበዓሉ ግርማ ጋር ምን ምን እንደተነጋገርን አንብባችኋል። ዛሬም የመጨረሻው ክፍል ይቀጥላል። እንዳነበባችሁትም እንደ ልቤ ስጠይቀው፣ እንደልቡ መልሶልኛል። እናንተም እንዲሁም ብትጠይቁት ይመልስላችኋል… በሉ! አሁን ከእናንተ ጋር ይብቃኝና እሱን ላነጋግርበት።
ጥያቄ። እሺ ጋሽ በዓሉ፣ ባለፈው ሳምንት የጀመርክልኝን ጨዋታ ዛሬ ጨርስልኛ! ባለፈው ትንሽ ቆይተህ ረጋ በልና አጫውተኝ ብልህ እምቢ ብለህ ቸኩለህ ሄድክ። መቸም ሁሌም እንደተጣደፍክ ነው። ያለ ድርጊት ውለህ ማደር እማትችል ይመስል ትሮጣለህ። እስቲ በሞቴ አሁን ምን አስሮጠህ?
ሩጫ ላይ ያለች ሀገር ናት። ቢከፋም ቢለማም ድርጊት። አዲሱ ትውልድ የድርጊት ትውልድ ነው። ጊዜ ያጥረናል። ጊዜ የለንም ችኩል ትውልድ ነን። ያበደ ትውልድ። እብዶች ነን እውነት። ያሮጌው ትውልድ ሙጣጭ ፣ ያዲሱ የበኩር ልጅ፣ ያንዱ መጨረሻ፣ የሌላው መጀመሪያ መሆን እብደት ነው ያሮጣል።
ኦሮማይ፤ ገጽ 8
ጥያቄ። እስቲ በል እንደ አባባ ስብሐት ገራም ገራሙን እንጫወት። ስለ ፍቅር አጫውተኝ? መቼም ፍቅር ልብህን ሳያጠፋው አይቀርም። የሀገር ፍቅር አለህ፤ የሰው ፍቅር አለህ፤ የኪነት ፍቅር አለህ። ብቻ ምናለፋህ ፍቅር ባለበት ቦታ ሁሉ የምትጠፋ አይመስለኝም።
ፍቅር የሕይወት ምንጭ፣ የሕይወት ቅመም ነው። ለሰው ልጅ፣ ፍቅር እንደ እንጀራ እንደ ውሃ እንደ አየር ያስፈልገዋል። ስንት ሚሊዮን ሰዎች በየምሽቱ ፍቅርን ፍለጋ በጨለማ ውስጥ እንደሚደናበሩ… ስንቱ ፍቅር አጥቶ በደረቁ ሌሊት ሲያፈጥ ሲያቃስት፣ ሁሉም ስለ ፍቅር ያስባል፣ ያደርጋል። ግን ማንም ስለ ፍቅር መናገርና መጻፍ አይፈልግም። ጤናማ አመለካከት አይደለም። ፍቅር ህይወት ነው። የህይወት ምንጭ ነው። እኔ ስለ ፍቅር አዜማለሁ፣ እዘፍናለሁ፣ እጽፋለሁ።
ደራሲው፤ ገጽ 75
ጥያቄ። እውነትህን ነው። ማንም አይፈልግም። አንተ ግን አዚመኻል- ዘፍነሃል-ውብ አድርገህ ጽፈሃል። እነ ሉሊት እና አበራን- ሂሩት እና ደርቤን – ሀዲስ እና ዓይናለምን- ሲራክ እና ማርታን- ሲራክ እና ጽጌን- ሲራክ እና ሰብለን እንዲሁም ፀግሽ እና ሮማንን ከሁሉም በላይ ደግሞ ፀግሽ እና ፊያሜታ ጊላይን ከፍቅር ገንዳ አስገብተህ እንዲንቦራቹ አድርገኻል። ይሁን እንጂ ሳሙኤል ቤኬት ጀምስ ጆይስ ስለ ተባለው ጸሓፊ ሲናገር ‹‹His writing is not about something; it is that something itself” ብሎ ነበርን ሰምቻለሁ። ታዲያ አንተም እንዲሁ ትመስለኛለህ። ለምሳሌ ፍቅርን ከነጓዙ ጠቅልዬ ካላሳየሁ ሞቼ እገኛለሁ ብለህ ታስቸግር ነበር። ስለ ፍቅር ሳይሆን፣ ፍቅርን ራሱ ካልጻፍኩ ብለህ፣ ልክ እንደ አባባ ስብሐት፣ ወሲብን ገሀድ ለማውጣት፣ ፍትወትን ፈትፍተህ ልታጎርሰን፣ ጥረህ እንደ ነበር አውቃለሁ። በሳንሱር የታነቀው ጉሮሮአችን ግን ፍትፍትህን አልዋጠልንም። ለመሆኑ ስለፍትወት ያለህ አመለካከት ምንድነው? ፍትወት፣ ፍትወት የሚያስብልህ ምክንያት ምንድነው?
ተፈጥሮ መፈንደቅ የምትጀምረው አበቦች ሲፈነዱ ነው። አበባ ፍትወት ነው። ውበት ነው። ወንድና ሴት ለአቅመ አዳም ሲደርሱ፣ ፍትወት ሲያምራቸው፣ ገላቸው ፍትወት መጎምዠት ሲጀምር ነው ውበት የሚጨምሩት፣ የደስታ ዜማ የሚያዜሙት። ወንድ ጡንቻው ሲያብጥ፣ ሴት አጎጠጎጤ ስታወጣ፣ አቤት ማማራቸው! ጠረናቸው ከሩቅ ይጣራል። ትንፋሻቸው እንደ እሳት ምላስ ከሩቅ ይለበልባል። ፍትወት ያስፈነድቃቸዋል። ያስቦርቃቸዋል። ያቁነጠንጣቸዋል። ሰው ፍትወት ሲጎመዥ አቤት ማማሩ፣ ሕይወት ያኔ ነው የምትጣፍጠው። አቤት ሕይወት ስትጣፍጥ በወጣነት ጊዜ። ሽማግሌ እንኳ ፍቅር ሲይዘው ይወበራል። ፍትወት የሕይወት፣ የደስታ ፣ የውበት ምንጭ ነው።
የቀይ ኮከብ ጥሪ፤ ገጽ 146
ጥያቄ። ታዲያ ኅብረተሰቡ ስለዚህ ምን የሚያስብ ይመስልሃል?
ኅብረተሰቡ ግብረ ሥጋን ያደርጋል እንጂ፣ ስለ ግብረ ሥጋ ማንበብና መስማት አይፈልግም።
የቀይ ኮከብ ጥሪ፤ ገጽ 105
ጥያቄ። ታዲያ ኅብረተሰቡ እማይፈልግ ከሆነ አንተ ምን ቸገረህ? ይልቅ ኅብረተሰቡ መስማት ስለሚፈቅደው ለምሳሌ ስለ ችግር ስለ ብቸኝነት… ለምን አትጽፍም?
ስለ ችግርና ስለ ብቸኝነት ለመዝፈን ፍላጎት የለኝም። መጻፍ የምፈልገው ስለ ዓለም ውበትና ስለ ሰው ተፈጥሮ መሠረታዊ ጥሩነት፣ እንዲሁም ሰው በራሱ የራሱን ደህንነት እንዳያገኝ ስለሚያደናቅፉት ሁኔታዎችና አካባቢዎች ነው። በዚህ ውስጥ ግን ችግርና ብቸኝነት አነስተኛውን ስፍራ ይዘው ይገኛሉ።
ከአድማስ ባሻገር፤ ገጽ 49
ጥያቄ። ስለዚህ፤ ስለ ውበት ብቻ ዝም ብለህ መጻፍ ትፈልጋለህ ማለት ነው። ውበት ደግሞ ፍቅርን ያመነጫል። ታዲያ ሁሉ ሰው ለፍቅር ቦታ ያለው ይመስልሃል?
ለፍቅር ቦታ የሌለው ልብ የለም። የሚከፍተው ጥሩ ቁልፍ አጥቶ እንደሆን?…
ደራሲው፤ ገጽ 62
ጥያቄ። ታዲያ አንድ ሰው ልቡ ለፍቅር ቦታ እንዳለው በምን ሊያውቅ ይችላል? አይ የእኔ ነገር ፣ አንዳንዴ ጠንቋይም ላደርግህ ይቃጣኛል። እማይጠየቅ ጥያቄ እጠይቅኻለሁ። ይኸውልህ ማለት የፈለግኩት ምን መሰለህ፣ ፍቅር ሲይዝ እንዴት ነው የሚያደርገው?
ፍቅር ለራሱ እውር ሆኖ እውር ያደርጋል ይባል የለ! ሁሉን ነገር ቆንጆ፤ ውብ አድርጐ ያሳያል። በፍቅር ዓይን፣ ዓለም የጽጌረዳዎች እቅፍ ትሆናለች። ማንኛውም ድምፅ ወደ ጥዑም ሙዚቃ ይለወጣል፤ ዝግ ያለ አሳዛኝ ሙዚቃ። ኀዘን በተሞላበት ሁኔታ ውስጥ ደስተኛ መሆን ይመጣል። በፍቅር ዓይን የማይታመነው ነገር ደግሞ ያጠራጥራል፤ ያነጫንጫል፤ ያናድዳል። ፍቅር ወደ ልጅነት ይለውጣል። ውብ ልጅነት ወይስ ውብ ጅልነት?
ኦሮማይ፤ ገጽ 207
ጥያቄ። እኔ ምን አውቃለሁ አንተው መልሰው እንጂ!?
አንድ ወንድ ስለ አንዲት ሴት ሳያቋርጥ ማሰብ ሲጀምር ፍቅር ይዞታል ወይም ሞኝ ሆኗል ለማለት ይቻላል።
ኦሮማይ፤ ገጽ 283
ጥያቄ። ከሞኝነት ሌላ በውስጣችን ሌሎች እንስሳዊ ስሜቶች የሉንም እንዴ?
የሰው ዘር ሞኝ ነው። ጅል ነው፤፡ ለሚኖረው አጭርና ጅል ሕይወት ገና ለገና የማሰብ ችሎታ አለኝ ብሎ ለእንስሳ ባሕርይው የረቀቀና የላቀ ትርጉም ሊሰጠው ይሞክራል። የስቃዩ ዋነኛው ምንጭ ይኸው ነው።
የቀይ ኮከብ ጥሪ፤ ገጽ 228
ጥያቄ። እንግዲህ እንዳንተ አባባል ከሆነ፤ የሰው ልጅ ለእንስሳትነቱ ገላጭ ባሕርይ ብዙ መጨነቅ ወይም ማሰብ የለበትም። ሕይወት አጭር ስለሆነች ዝም ብሎ ተጃጅሎ መኖር አለበት ማለት ነው። እንደ’ኔ ደግሞ፤ ሕይወት ከዚህም በላይ ትመስለኛለች። በተለይ ‹‹ዕድል›› በሕይወት ውስጥ ያለው ቦታ ከፍተኛ ነው። የዕድሉ ዕጣ ዓይነት ይለያይ እንጂ ያለ ዕድል የሚኖር የለም። ዕድል ሁሉ ደግሞ አይቀናም። ያልቀናቸውን ትተን፣ ስለቀናቸው እንኳ ብንነጋገር፣ የቀናቸው ያወቁበት አይመስሉም። ስለዚህ ዓይነቱ ነገር ምን ትላለህ?
በዚህ ዓለም ቀንቶአቸው ሊኖሩ የሚችሉት በገጠማቸው ዕድል ያለ ምንም ማመንታትና ማወላወል ለመጠቀም ወደ ኋላ የማይሉት ብርቱዎች ናቸው። የቀረነው የሕይወት አጫፋሪዎች ነን።
ሀዲስ፤ ገጽ 207
ጥያቄ። እሺ ይሁን ማጫፈሩንስ እናጫፍር፤ ግን ያልገባኝ ነገር፤ ብርቱ ስትል ምን ማለትህ ነው? ብርታት በምን ይገለጻል? በብልህነት? በጥንካሬ? ወይንስ በሀብት? እነዚህ ቃላት ራሳቸው እንኳ ለእኔ ግልጽ አይደሉም። እስቲ ስለ ብልህ፣ ስለ ጥንካሬ ስለ ሀብታምነት፣ ስለ አዋቂነት ያለህ አስተያየት ምድነው?
አንድ ሊቅ… ማነው ብልህ ቢሉት ‹‹ከእያንዳንዱ ሰው ሊማር የሚችል፤ ማነው ጠንካራ ሰው ቢሉት ስሜቱን መቆጣጠር የሚችል፤ ማነው ሀብታም ቢሉት፣ በቃኝን የሚያውቅ፤ ማነው የተከበረ ቢሉት ሰውን የሚያከብር›› ብሎ መለሰ ይባላል።
ሀዲስ፤ ገጽ 22
ጥያቄ። ሌሎቹ ይሁኑ ግድ የለም፣ ግን ‹‹በቃኝ››ን የሚያውቅ ሰው ሀብታም ነው ስትለኝ አልገባኝም። ለምሳሌ፣ እኔ አሁን ምንም የለኝም። ሌላውም እንዲሁ የሚል ይመስለኛል። ሁላችንም’ኮ ‹‹ነገን›› የምንጠብቀው የሌለንን ወይም ያልተሟልንን ይዞ ከች እንዲልልን ነው። በተለይ ደግሞ ገንዘብን። ገንዘብ ደግሞ ይቆጠራል። ቁጥር ደግሞ መጨረሻ የለውም። መጨረሻ እንኳ ቢኖረው ጥሩ፤ ሰው በቃኝ ሊል ይችላል። ታዲያ ይኼ እንዴት ነው የሚሆነው? ወይስ ገንዘብ የሚባል ነገር ጨርሶ አያስፈልግም ማለትህ ነው?
ያለ ገንዘብ፣ ሰው ሰው አለመሆኑን አይቻለሁ.።… ሕይወት ያለ ገንዘብ ምን ዋጋ አላት? አየህ ዓለም ብዙ የሚያጓጉ ቆንጆ ቆንጆ ውብ ነገሮችን ይዛ ፊትህ ላይ ስታስደንስ ትውላለች። ታዲያ ያለ ገንዘብ አይገኙም። ያለ ገንዘብ የሕይወት ውብ ነገሮች አይገኙም። ግሩም ሻይ ያለው ይጠጣል፤ የሌለው ያፈጣል እንደሚባለው ነው።
ሀዲስ፤ ገጽ 95
ጥያቄ። አዎ ምንታደርግ ተሳለቅብን እንጂ! ‹‹ያለ ገንዘብ፣ ሰው ሰው አለመሆኑን አይቻለሁ›› ትለን?! አንተ ግን ያለ ገንዘብ፣ ሰው ሰው መሆኑን ራስህ ሆነህ አሳይተሃል። ወይንስ ሰው አይደለህም? ለምን እንደ አንዳንዶች ለገንዘብ ብለህ አልጻፍክም፣ እናም አልኖርክም? ሁሉን መውደድ ምን ዋጋ አለው ብለህ ነው?
ሁሉን ትወዳለህ በመጨረሻም ሁሉንም ታጣለህ። ሴላቪ ኦሮማይ!
ኦሮማይ፤ ገጽ 370 የመጨረሻው ዐረፍተ ነገር
በጣም አመሰግናለሁ። ኦሮማይ!
መስከረም 17 እና 24 1984፣ በ‹‹የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ›› ጋዜጣ ላይ ታተመ። ጸሀፊው ደረጀ ደስታ ነው።
Subscribe to Ledesta
New writing in your inbox. English and Amharic.