
ወጣቶቹ “ምንድነው ዝምታው” የተሰኘውን የዘሩባቤልን ውቤ ዜማ፣ “ይደገም ቢስ ቢስ (ይደገም ይደገም)” እያሉ ነው።
ወጣትነት እኮ ጥሩ ነገር ነው። ህይወት እዚያችው ናት። ዘፈን እንኳ ሳይቀር “ይደገም” ያሰኛል። ቆይ ግን፣ ሁሉሽም አድገሽ እኔ እድሜ ስትደርሺ፣ ዘፈን ሳይሆን “ህይወት ይደገም ወይስ አይደገም” እያልሽ ማሰብ ትጀምሪያለሽ። ወይም “ይኸኛው ህይወት በቅቶ የላይኛውን ደግሞ ባየነው” ትያለሽ። ወይም ደግሞ “ይኸኛው ህይወት ራሱ ቢደገምስ እያልሽ ዘመንሽን ታዜሚያለሽ።
…እንደገና መውደድ እንደገና
እንደገና ፍቅር እንደገና…
አዎ፣ ምክንያቱም ሞት ይመጣላ!
መሀሙድ አህመድ “እንደገና ፍቅር እንደገና” ሲል “አይገኝምና” የሚለውን እያሰመረበት ነው። ህይወት መረረች ጣፈጠችም ውሏ አንዴ ነው። መሀሙድ “ለምን ታኮርፊያለሽ ፈገግታ ስጭኝ” እያለ እንዳዜመው፣ ህይወት በኩርፊያ አትሆንም። መኖር እስክምናምኗ ታጓጓለች። ምክንያቱም ማለፍ አለ። በዚያው ወስዶ የሚያስቀር ነገር አለ። ስለዚህ ዳግመኛ ህይወትን መመኘት ያለ ነው።
“ሞት እንኳ ደጋግሞ ….ከሚያስቀር
ምናለ ደጋግሞ …ቢፈጠር…”
— ይላል የጥላሁን ገሠሠ ዜማ።
የሌላው ህልፍት በሀዘን የሰበረህ፣ አንተንም እንዲሁ ስጋት የበረበረህ ቀን፣ ስለራስህ ማሰላሰልህ አይቀርም። ትዘፍነው ብታጣ ያነበብከውን ትመዛለህ። ምናልባት የፍሬድሪክ ኒቸ ፍልስፍና ትዝ ይልሃል።
“the eternal recurrence of the same።” ይህ ሀሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ኒቸን የመጣበት እ.ኤ.አ. ነሐሴ 1881 ነበር — በስዊዘርላንድ አልፕስ ተራሮች መካከል ሲራመድ፣ እንደ ፒራሚድ ከፍ ብሎ የቆመ ትልቅ ድንጋይ አጠገብ ቆሞ ሳለ ነው ሀሳቡ የመጣለት። ወረቀት ላይ ጻፈው። ኒቸ ይህን ሀሳብ በተለይ በዛራሱስትራ አማካይነት፣ ከዚያም በፊት “የጌይ ሳይንስ” በተባለው መጽሐፉ ውስጥ ነው ያዳበረው — የሰው ልጅ ህይወቱን አንስቶ እንዲመረምራትና ትርጉም እንዲሰጣት የጠየቀበት ጽሁፍ።
የኒቸ ጥያቄ እንዲህ የሚል ነው፦ “አሁን የኖርካትን ህይወት አንዷንም ነገር ሳታጎድል ተመልሰህ ኑራት ብትባል ትቀበላለህ?” ልብ አድርግ ሁሉም ነገር እንዳለ ይደገማል ይልሃል።
ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ ከነበርክ፣ ንጉሡ ከሥልጣን ይወርዳሉ። ደርግ የረሸናቸው ሰዎች እንደገና ይረሸናሉ። ወያኔዎቹ አዲስ አበባ ገብተው ግንቦት 20 ይላሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንደገና ወደ ሥልጣን ይመጣሉ። ትረምፕ እንደገና ይመረጣሉ። በአንተ እድሜ የሆነው ሁሉ እንደገና ተመልሶ ይሆናል።
በግል ህይወትህ የሆነው ሁሉ ይሆናል። ቤተሰቦችህ ይወልዱሃል። ጡት ትጠባለህ፣ ትድሃለህ፣ ትምህርት ቤት ትሄዳለህ ትመጣለህ፣ ትምህርት ትጨርሳለህ፣ እዚያቹ መ/ቤት ሥራ ትገባለህ፣ ገርልፍሬንዶችህን ሁሉ እንደገና ትይዛለህ። ታገባለህ የወለድካቸውን ልጆች ራሳቸውን ትደግማለህ። የሞተብህ ሰው ካለ አሁንም ካንተ ጋር ኖሮ ይሞትብሃል።
በልጅትነትህ እየቧረቅህ የተጫወትከው፣ የተጫወትሽው፣ የጉርምስና ዘመን ዳንስ፣ ፍቅሩ ተጨማምቆ መተቃቀፉ፣ ለብ ባለ ትንፋሽ የተሞላው የአፍ ለአፍ መጎራረሱ፣ ጃን ሜዳን የሚያኸለው አልጋ አልበቃ ያለበት የፍቅር ፍልሚያ፣ የሠርግሽ እለት አሁን ደመቅሽ አባብዬ፣ ሙሽራዬ የተባልሽበት፣ ሙሽራው “ሀይ ሎጋ!” ስትባል የተጀነንክበት፣ ልጆችህን በደስታ ተሞልተህ በሳሳ አንጀት የተመለክትባቸው ቅጽበቶች፣ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ኦሎምፒክ ያሸነፈበት እለት፣ ለብዙ ዘመን የናፈቅከውን ወዳጅህን ያገኝህበት፣ እነዚህና ሌሎች የፈንጠዚያ አጋጣሚዎች ሁሉ ይደገማሉ።
እያንዳንዷ ቅንጣት ህይወት ትደገማለች። የካቲት 17/ 1986 ማክሰኞ ከጧቱ 4ከ25 ልክ ሽንት ቤት እንደተመጥቅክ የተለቀቀች ፈስ እንኳ ትደገማለች። የዋሸሃት ውሸት አትቀርም። ያታለለህ ሰው መልሶ ያታልልሃል። የደበደበህ ሰው መልሶ ይንረተሃል። የያዘህ በሽታ መልሶ ይይዘሃል።
ጸጸት እና ቁጭት ሳይቀሩ ይደገማሉ። እንዲህ ቢሆን ኖሮ፣ ይህን ባደርግ ኖሮ፣ ይህን ባላደርግ ኖሮ፣ ይህን ሰው፣ እሱን እሷን ባላገባ ኖሮ፣ እዚህ ሀገር፣ ከዚህ ቤተሰብ ባልወለድ ኖሮ፣ በዚህ ዘመን ባልፈጠር ኖሮ፣ የሚሉ ከንቱ ጸጸትና ቁጭቶችም ይደገማሉ። ወጣት መሆንስ አሁን ነበር እያልክ፣ አሁን የማወቀውን ያኔ ባውቅ ኖሮ እንዲህ አደርግ ነበር፣ እያልክ የምትቆጭና የምትመኝባቸው ነገሮች ሁሉ ምኞት ሆነው ይደገማሉ። በየአጋጣሚው የተዋወቅካቸው በየጊዜው ያንጠባጠብካቸው፣ የቀርብካቸው፣ የሸሸሃቸውን ሁሉ እንደገና ትደግማቸዋለህ። በዚህ ትስማማለህ?
ቢስ ቢስ፣ ይደገም ይደገም!…
ልብ አድርግ ዳግም መፈጠርን ስትመኝ ግን በገባኸው የግዴታ ውል መሰረት ነው። ምንም የምትለውጠው ይቺን ይቺን እንኳ ላስተካክላት የምትላት አንዲትም ቅጽበትም አትኖርም። ላድርግም ብትል አትችልም። ምክንያቱም ድጋሚ መሆኑን አታውቀውም። ይህን ሁሉ አውቀህ ነው የምትገባበት። በቃኝ ሰለቸኝ ሳትል ይህን እየደጋገምክ ለዘለዓለም ትኖራለህ። ማለትም ይህን ለዘለአለም ኖረህ ሞተህ እየተነሳህ ታደርገዋለህ። ይህ ህይወትህ ዝም ብለህ እየደጋገምክ ለዘላለም የምትኖረው ህይወትህ ይሆናል። በዚህ ትስማማለህ?
“ከሞትክ በኋላ ምን መሆን ትፈልጋለህ?” ብትባል፣ በዚያው ልቅር ግድ የለም ትላለህ ወይስ የላይኛውን ቤት ትኬት ከወዲሁ ገዝተሃል። ወይስ ኒቸ በምኞት እንዳጎነጻፈህ፣ ደግሜ፣ ደጋግሜ፣ ተደጋግሜ እየሞትኩ፣ እየተለወለድኩ ያንኑ ህይወት እየደገምኩ፣ እየተደገምኩ…ያለማቋረጥ ዙሩን.. ለዝንተ ዓለም እቀጥላለሁ ባይ ነህ።
ደግነቱ ኒቸ ሀሳቡን ያመጣው ስላለፈው ህይወት አይደለም። ስለ አሁኑና ካሁን በኋላ ስላለህ ህይወትህ ነው። ዛሬ መኖር ያለብህ ነገ ልትደግመው እምትፈልገውን ህይወት መሆኑን ሊያሳስብህ ነው።
ለዚህም “amor fati” (የእጣ ፈንታ ፍቅር) የሚል ስም አለው። ህይወትህን እንዳለች ሙሉ በሙሉ ወደህ፣ እንደገና በደስታ ለመቀበል መዘጋጀት ማለት ነው።
ወዳጄ ሆይ፣ ከዚህ በኋላ ባለች ህይወትህ፣ እያንዳንዷን ቀን ስትኖራት ነገ ልትደግማት እንደምትሻ እርግጠኛ መሆን አለብህ። ልክ ነገ ብቻ ሳይሆን መላልሼ እኖረዋለሁ እያልክ መኖር ይኖርብሃል። የኒቸን ፍልስፍና አልፎ አልፎም ቢሆን ተጫወትባት።
ማን ያውቃል፣ ድጋማት የተባልካት እንደሆን አይጸጽትህም።
በነገርህ ላይ ምንጩን አትጠይቀኝ እንጂ “ቢስ” ማለት “ይደገም” ማለት ነው። የሀበሻ ነገር ደግሞ ያው እንደምታወቀው ነውና ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ያው ቃል ሌላ ትርጉም አለው ይልሃል። ለምሳሌ ዋጋ ቢስ፣ እርባና ቢስ፣ ቀልበ ቢስ … ስትል ቢስ ማለት ባዶ አልቦ አይረባም ብላሽ ምንትስ ሊሆን ወይም ሊመስል ይችላልል።
እና ህይወትህን “ቢስ ቢስ” ስትል ይደገም (ይረባል) ወይም ቢስ (አይረባም) እያልክ ስለመሆኑ ለይተህ ተናገር። ማለቴ.. እየለየህ ኑር፣ ወይም ኑሪ። አንተም አንቺም እያንዳንድሽ!
ይህ ጽሁፍ በመጀመሪያ በአማርኛ በለደስታ ላይ ታትሟል።
Subscribe to Ledesta
New writing in your inbox. English and Amharic.