
‹‹ያን ወንበር አየኸው?››
‹‹የቱን?››
‹‹አንድ ወንበር ነው ያለው!››
‹‹አዎ አየሁት?››
‹‹ምንድነው?››
‹‹ወንበር!››
‹‹ወንበር ከምን ከምንድነው የሚሠራው?››
‹‹ከእንጨት?››
‹‹ማን ይሰራዋል?››
‹‹አናጺ››
‹‹ማን ይቀመጥበታል?››
‹‹ሰው››
‹‹ስለዚህ ለወንበር ወንበርነት፣ እንጨቱ አንድ፣ አናጺው ሁለት፣ ወንበሩ ላይ የሚቀመጥ ሰው ሦስት — እነዚህ ሦስት ነገሮች መኖር አለባቸው?››
‹‹አዎ፣ መሰለኝ።››
‹‹ካለ እነዚህ ሦስት ነገሮች ወንበር ሊኖር ይችላል?››
‹‹አይችልም።››
‹‹ስለዚህ የወንበር ወንበርነቱ ምኑ ላይ ነው?››
‹‹አልገባኝም።››
‹‹እነዚህ ባይኖሩ፣ ወንበር የሚባል ነገር የለም።››
‹‹ስለዚህ የሰው ሰውነቱ ምኑ ላይ ነው እንድልህ ነው?››
‹‹እንደሱ አላልኩም።››
‹‹በዚህ ተጠየቅህ እስኪ ሰውን ግለጸው።››
‹‹ሰው እንደ ወንዝ ነው።››
‹‹ወንዝ ምንድነው?››
‹‹አንድ ነገር አይደለም፣ ወንዝ ውሃ ነው፣ ወንዝ ተንቀሳቃሽ ነው፣ ወንዝ በየሰከንዱ ይቀያየራል።››
‹‹ይህን ከሰው ምን ያገናኘዋል?››
‹‹ሰው ነህ፣ ከተሠራኽባቸው ነገሮች ተሰርተሃል። ደርቀህ አልቀረህም ወይም አልረጋህም። ትንቀሳቀሳለህ። ትለዋወጣለህ። ስለዚህ አንድ ነገር ብቻ አይደለህም። ይህን ሁሉ ሆነህ ግን አሁንም አንተው ነህ።››
‹‹ይህን የማወቅ ጥቅሙ ምድነው?››
‹‹አየህ ስታስብ፣ ሁልጊዜ ልክ ነኝ ወይም መሆን አለብኝ አትልም። ለዘላለም የሚጸና ነገር የለም። ይህ ነገር/ይህ ችግር ይገልጸኛል አትልም። ነገሮች እንደምታስባቸው ባሉበት የሚቆዩ ሳይሆኑ ተለዋዋጭ ናቸው። የሚለያዩም ሳይሆን ልክ እንደ ወንበሩ ከተለያዩ ነገሮችና ሁኔታዎች የተሠሩ ስለሆኑ ተያያዥ ናቸው። ሁነት የብቻ አይደለም።››
‹‹ሁሉ ነገር የሚቀያየርማ ከሆነ ምን ዋጋ አለው?››
‹‹ምንም። ዋጋ የለውም፣ ባዶ ነገር ነው።››
‹‹ነገሮች ተያያዥ ከሆኑ እንዴት ባዶ ይሆናሉ?››
‹‹ያያያዟቸውን ነገሮች ብታወጣቸው ባዶ ይሆናሉ።››
‹‹ስለዚህ ሁሉ ነገር እንደ መኪና የተገጣጠመ ነው ማለት ነው?››
‹‹ደሬ፤ እኔ ናጋርጁና ነኝ። ከቡድሃ በኋላ የመጣሁ ትልቁ ቡድሃ፣ በኛ ዘመን መኪና የለም።››
‹‹ኮምፒወተርም አልነበረም?››
‹‹ምንድነው ደግሞ እሱ?››
‹‹ማሽን ነው፣ በባይነሪ ቁጥሮች እያሰላ የሚሰራ የዘመናችን ማሰቢያ ነገር።››
‹‹እኔ እሱን አላውቅም። በኛ ዘመንም ቢሆን ግን፣ ሰዎች ነገሮችን በሁለት እየከፈሉ (በባይነሪ) ያስባሉ።››
‹‹ምን እና ምን እያሉ?››
‹‹መኖር ወይም አለመኖር፤ እውነት ወይም ሀሰት፤ እኔ እና ዓለም፤ እኔ እና ሌሎች…›› እያሉ።
‹‹እሱ አስተሳሰብ ችግር አለበት።››
‹‹ምን ዓይነት ችግር?››
‹‹አንደኛ፣ ነገሮች ዘለዓለማዊ ናቸው። ሁለተኛ፣ ነገሮች ምንም ነገር አይደሉም። ባዶም ናቸው።››
‹‹ሁለቱ አይቃረኑም?››
‹‹ይመስላሉ፣ ግን አይጋጩም። ዝም ብለው የዕውቀት ሱስ ናቸው።››
‹‹ታዲያ ምን ይሻላል?››
‹‹’መካከለኛው መንገድ’ የተባለውን መያዝ።››
‹‹እውነታ ሲባል ታዲያ ምንድነው?››
‹‹ምንም።››
‹‹ሊሆንማ አይችልም?››
‹‹በላ እንግዲህ ራስህ እውነታህን ውሰደው፣ በተጠየቅ መርምረው፣ በራሱ ሄዶ ሄዶ እብስ ሲል እየው።››
‹‹አቅልለው እስኪ?››
‹‹ቅድም እኮ ወንበሩን አየነው። ወንበር ያለ እንጨት፣ ያለ አናጢ እና የሚቀመጥበት ሰው ምንድነው?››
‹‹ምንም።››
‹‹ይህንን ተጠየቅ ወስደህ ጊዜን፣ ራስን፣ እንቅስቃሴን፣ ምክንያታዊነትን፣ ራሱ ቡዲዝምንም ቢሆን እየው።››
‹‹ስለዚህ ምን እያልክ ነው ናጋርጁና?››
‹‹ነገሮች ያሉት በምክንያት ነው። ያለ ምክንያትና ሁኔታዎች ባዶ ናቸው። ስለዚህ ባዶነትን ተቀበል።››
‹‹ባዶ ነህ እያልከኝ ነው?››
‹‹አይደለም። አካልህን፣ አዕምሮህን፣ ሀሳብህን አይደለህም። ከምክንያትና ሁኔታዎች የተነጠልክ ወይም ከእነሱ ጋር አንድ ዓይነት የሆንክ ነገርም አይደለህም።››
‹‹ይህም እኮ ባዶነት ነው!››
‹‹አንተ ሰው ከባዶነት ጋር ችግርህ ምንድነው? ባዶነት ዋጋ የለውም ብለህ ከሆነ ተሳስተሃል። ስጋት ቀፈህ፣ ኮተት አራግፈህ፣ ባዶነትህን ስትቀበል ይበልጥ ትሁት፤ ይበልጥ ጥሩና የተረጋጋህ ሰው ትሆናለህ።››
‹‹እና ታዲያ ምን ላድርግ?››
‹‹ተቀበል። ከነገሮች ተሰርተህ ከነገሮች አትነጠል፣ ህይወት ሂደት፣ ግንኙነት፣ ፍሰት ናት። አብርሃት ፍሰስ።››
‹‹ምን ዓይነት ጣጣ ነው — ከወንዝ ጋር ፍሰስ፣ ከነፋስ ጋር ንፈስ!…››
እስካሁን ሲታዘበኝ የቆየው እግዚአብሄር ‹‹ነፋስን እንደ መከተል ነው…›› ሲል ያንሾካሾከ መሰለኝ።
የሱ ነፋስ ከየት ይነፍስ፣ ወዴት ይነፍስ… አለመታወቁን ለመግለጽ ሊሆን ይችላል። ቢያውቁትስ ምን ይረባል። አሁን ይኸው ከመታወቁም አልፎ ከቀናት በፊት የሚተነበይለት የአሜሪካ ነፋስ ቅጠል ሳይሆን ሰው ያወዛውዛል። ሲሻውም ይቆጣል። ጸጉር ልንጠቅ፣ ከደጅ ያለ ዕቃ ልገለባብጥ ይላል። መስኮት ይደረግማል፣ በር አጩኾ ይዘጋል። ግንብ ይደረምሳል፣ ቤት ያፈርሳል፣ ዛፍ ይገነድሳል። አሁን ከሱ ዓይነቱ ነፋስ ጋር እንዴት አብሮ ይነፈሳል?
በህንድ የቡዲስቶቹ ‹‹ሙላመድያ መካከሪካ›› (Mūlamadhya makakārikā) መጽሐፍ ጸሐፊ ናጋርጁና (Nāgārjuna)፤ ዛሬ ቢኖር ኖሮ ስለ ከባድ ዝናብም ሆነ ጎርፍ ምን ሊል ይችል ነበር? ያለ ምንም ጥርጥር፣ በሱ ፍልስፍና ጎርፍ ውሃ ብቻ አይደለም። የብዙ ነገሮች ድምር ነው። ፖሊሲ፣ የኮንስትራክሽን ጉዳይ፣ ቸልተኝነት የመሳሰሉት ሊሆኑ ይችላሉ። ጎርፍ ውጤት ነው። ቢሆንም ቢሆንም ይህ አስጨንቆህ ከሆነ የጭንቀትህ ምንጭ በተለዋዋጩ ዓለም ዘለዓለማዊ ሆነህ መኖር መፈለግህ ነው። ይልቁንም፣ ሁሉም ነገር የሚሰራው ከሌላው ነገር እንደ መሆኑ መጠን፣ ከጎርፉ አደጋ የሚያተርፍህ፣ ስለ አደጋው የሠራኸው የመከላከል ዝግጁነት ነው። ናጋርጁና በተስፋ የሚኖር ወይም በጽልመት የሚያበቃ ሰው አይደለም። ዝግጁነት ኖረም — አልኖረም፤ ማዕበል መምጣቱ አይቀርም ይላል።
እውነቱን እኮ ነው አልኩ። ችግር አይቀሬ ነው። ‹‹ችግርን ማስቀረት እንዴት ይቻላል?›› ብዬ ልጠይቀው አስቤ ተውኩት። ታውቆ በቀጠሮ የሚመጣ ከሆነማ ምኑን ችግር ሆነው? ሊለኝ ይችላል።
Subscribe to Ledesta
New writing in your inbox. English and Amharic.