
ያው ደግሞ ተኮራርፈዋል መሰለኝ። በጨዋታችን መካከል ጓደኛዬ ጓደኛችንን ሲያማልኝ እንደዚህ አለ። ” እኔ እኮ የአገር ጉዳይ ሁኖብኝ ነው እንጂ ከሱ ጋር እኮ ጠብ የለኝም። እንዴ አንተም ታውቃለህ፣ ከሱ እሚበልጥ ጓደኛ ማን አለኝ?”
“አገር ነዋ! አገር ከሱ ትበልጣለች?” ብዬ የቀልዴን ላጅበው አልኩና ተውኩት! እኔ እምለው ግን፥ አገር ከጓደኛ ትበልጣለች እንዴ?
ይቺ አገር እምትባል ነገር አንዳንዴስ ትደንቃለች። ጓደኛን ሳይቀር አስጠልታ፣ በትውልድና ብሔር አባልታ፣ ስታኮራርፍ ምንም አይመስላትም። ይቺ አገር እምትባል ነገር ምን ጉድ ነች?
እና ጓደኛዬ እነገሌን ደገፈ ወይም ነቀፈ ተብሎ “በአገር የመጣ በኔ የመጣ ነው” ማለት ምን እሚሉት ነገር ነው? አንድ ነገር ግን ቆጨኝ። በጓደኛዬ የመጣ በአገር የመጣ ነው ብዬ ሳልቀልድበት ከጓደኛዬ ጋር ተለያየን።
ቀድሞ ነገር አንተ ራስህ እንደዚያ ያለ ሰው እንዴት በጓደኝነት ልትይዝ ቻልክ? ግን እንዳትሉኝ። አንዳንድ ጊዜ እኮ ጓደኝነት የዘለላለም እዳ ነው። አደገም ጎደለም እንደ አደራ እቃ ተጎለተም ያው ነው። ቀጣይ እንኳ ባይሆን ትዝታው ጣፋጭ ነው። ቢለወጥ፣ ባይለወጥ፣ ቢኖር፣ ቢከዳ፣ ቢሞት፣ ጓደኛ ጓደኛ ነው። በሀብት፣ በእውቀት፣ በፖለቲካ፣ በእምነት፣ አይለወጥም። አይደመርም አይቀነስም። እነ እገሌን ደገፈና ነቀፈ እንኳ ተብሎ ቢሆን “አንተ ደግሞ ከዚህ ሰውዬ ፍቅር ይዞሃል” ወይም “ይህን ሰው ጠምደህ ልትሞት ነው” ተብሎ ተሹፎበት ይታለፋል።… የዘንድሮ ጓደኝነት ግን…?
እንኳን በአገር ስም ብሄርና መንደር ተነካ ተብሎ ይታበዳል። ሀገርና ብሄር ጣልቃ ገብቶ ባልና ሚስትነትን አያስተቃቅፍም። እንኳን የህይወት አጋርን ከመንደር ያኳርፋል።
ለአገር ሲባል ህዝብ ተቀይሞ አኩሮፎ፣ አገር ቀርቅሮ፡ አቀርቅሮ፥ ተቀርቅሮ በየቤቱ የተቀመጠ ስንት ሰው አለ። ህዝብን እኮ እየቦጨቁ መዝናናት የጓደኝነት አንዱ ምስጢር ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን ጓደኛም ወይ ከመንግስት ወይ ከህዝብ ተደመረና ዐይንን ላፈር እየተባለ ይመስላል። አንዳንዶችም እንደ አብርሐም በግ ጓደኞቻቸውን ለአገር ጥቅም ሲባል በአደባባይ አሳልፈው ለመሰዋት ሲዘጋጁ ማየቱ ያስገርማል።
ለማንኛውም ይህ የተደመርና የተቀነስ ዘመን፣ ጓደኞቻችንን ይጨርስብን ይሆን? “በጓደኛችን የመጣ በአገር የመጣ ነው” አይባል ነገር፣ መከራ ነው። አንድም ሰው ሳይወደድባት፣ ብቻዋን እምትወደድ አገር ትቆጣለች። ከጥላቻው ብዛት አንድም እሚወደው ሰው ሳይኖር አገር ወዳድ እሚባል ሰው መኖሩ ደግሞ ሁል ጊዜም ያስደንቃል። ወዳጄ ሆይ ብትሰርቅም ብትቀጥፍም ሌላው ቀርቶ ብትገድልም እንኳ ምንጊዜም ጓደኛዬ ነህ። አልደግፍህ አልከተልህ ይሆናል። ምን አባቱ ሆኖ ነው ከማለቴ በፊት ግን ምን ነክቶት ነው ማለትን አስቀድማለሁ። አንተን ተሽቀዳድሜ አሳልፌ በመስጠት እማድነው አገር እምሸምተው ዝና አይኖርም። በአፍንጫዬ ይውጣ!!!!
Subscribe to Ledesta
New writing in your inbox. English and Amharic.