ከበደ ሚካኤል ምን ማለት ነው?

“በመጨረሻም እስኪ ይህን (ፊልም) ተመልከቱ፦

ይህ ፊልም የሚያሳየን ቀዳማዊው ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ በመጨረሻው ዘመናቸው፣ በቁጥጥር ስር ሆነው፣ በደርግ እስር ሳሉ ነው። የነበሩባትን ቤት ተመልከቱ። በዚህች ክፍል ከነበሩት አምስት መጻህፍት መካከል፣ ሶስቱ የክቡር አቶ ከበደ ሚካኤል ድርሰቶች ነበሩ። ፊልም አንሺው ጃንሆይ ወደ ነበሩበት ክፍሉ ሲገቡ ንጉሠ ነገሥቱ ያነቡት የነበረው መጽሀፍ “ሥልጣኔ ማለት ምንድነች?” የተባለውን የከበደ ሚካኤልን ድርሰት ነው።

ስለዚህ ሁኔታ አቶ ከበደ ተጠየቁ።

አፄ ኃይለ ሥላሴ በዚያ አሰቃቂ ሁኔታ ሳሉ፣ በቤተመንግሥታቸው ከነበሯቸው ብዙ ሺ መጻህፎቻቸው መካከል የርስዎን መጻህፍት መርጠው መውሰዳቸው እና በመጨረሻው ቀናቸው “ሥልጣኔ ማለት ምንድነች?” የምትለውን መጽሀፍዎን ያነቡ የነበሩት ለምን ይመስልዎታል?

“እኔ እንጃ እኔ አላውቅም። የሥልጣኔን አየርና ሥልጣኔ ማለት ምንድነች? የተባሉትን መጻህፍት ከጻፍኩ በኋላ ከጃንሆይ ጋር ተራርቀናል።”

ምን አራራቀዎት?

“ምክንያቱም ቀደም ሲል ጃፓን እንዴት ሠለጠነች የሚለው መጽሀፌን ጽፌ ስሰጣቸው ደጋግመው ካነበቡት በኋላ ‘ምነው ይህን ነገር ብትተወው እኛ የተጻፈን እናነባለን። ግን በተግባር አንተረጉመውም ስለዚህ በሥራ ላይ የማናውለው ስለሆነ መጽሀፍን አቁም’ ብለውኝ ነበር። እና እንግዲህ ያን ጊዜ ያሉኝ ትዝ ብሏቸው ይሆናል።”

ደራሲና ገጣሚ ኢንጂነር ታደለ ብጡል ክብረት ባዘጋጁት “የከበደ ሚካኤል ህይወት ታሪክ” ፊልም ውስጥ ነበር ይህን ያገኘሁት።

ጃንሆይ በዚህ ለከበደ ሚካኤል ህያውነት መታሰቢያ በተዘጋጀው ፊልም ውስጥ ሆነው ሲንጎራደዱና “ሥልጣኔ ማለት ምንድነች?” የተሰኘችውን የከበደ ሚካኤልን ድርሰት ከፊት ለፊታቸው ዘርግተው ይታዩ ነበር።

 

ከዚህ ጋር በተያያያዘ ሀያሲውና ደራሲው አስፋው ዳምጤ ያጫወቱኝ ተመሳሳይ ነገር ታወሰኝ።

በደርግ ጊዜ ነው። የሠርቶ አደር ጋዜጣ አንደኛ ዓመቱን ለማክበር ሽር ጉድ እየተባለ ነው። በዓሉን ደማቅ ለማድረግም ዘንድ ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን እና የርዮተ ዓለም መምርያው ኃላፊ ሽመልስ ማዘንጊያ አንድ ነገር ይመክራሉ። በበዓሉ ላይ ታላቅ የስነጽሁፍ ሰው በክብር እንግድነት እንዲገኝ በማሰብ ከበደ ሚካኤልን ይመርጧቸዋል።

“እሮሮ” የተሰኘው ግጥምም ይመረጥና እንዲነበብ ይታቀዳል። ከበደ ሚካኤልም ስለ ስነጥበብ ንግግር ያደርጉ ዘንድ ይታሰባል። ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ በጥሞና ተቀምጠው ንግግሩን ያደምጣሉ። ይህ ፕሮግራም ይታለምና ወደ ከበደ ሚካኤል ሁለቱም ተያይዘው ይሄዳሉ።

ከበደ ሚካኤልን ያገኝዋቸውና “እርስዎ የቀደመውን የስነ ጽሁፍ ዘመን ወክለው በቀድሞ ደራሲነትዎ ንግግር እንዲያደርጉልን በታላቅ ትህትና ጋበዘንዎታል…” ይሏቸዋል። ከበደ በደንብ ካዳመጥዋቸው በኋላ “ለመሆኑ የቀድሞ ደራሲ ስትል ምን ማለትህ ነው?” ይሉና ሽመልስን ይጠይቋቸዋል። “አያይ ከ66 በፊትና በኋላ ያሉትን ማለት ፈልጌ ነው” ይሏቸዋል። ከበደ በዚህ ጊዜ “አሃ አንተ ከ66 በኋላ ነዋ የተወለድከው?” በማለት ይጠይቃሉ። ወዲያው በማስከተል፦

“ሰማህ ወዳጄ — አንድ ደራሲ የቀድሞ የሚባለው ወይ ከሞተ፣ ወይም ደግሞ ብእሩ ከነጠፈ ነው። እንደምታዩት እኔ አልሞትኩም።”

“ይህን የተመከረ ማኒስክሪፕቴን፣ እኔ ከጻፍኳቸው 71 ሥራዎች ውስጥ 21 ምናምን ብቻ ነው የታተመው። ስለዚህ አሁን እሮሮን መርጠናል የምትሉኝ፣ እሱማ ምን አለው — እናንተ ተማሪ ሆናችሁ የተጻፈ ነው። አሮጌ ነገር ነው። ይልቅ የኢትዮጵያ ዛሬ የሚጠይቀው ከበደ ሚካኤል አለ ወይስ ሞቷል? ካለ ምን እየሠራ ነው ብሎ ነው።

ስለ ስነጽሁፍ ንግግር አድርግ በማለታችሁ በደስታ። ጥበብኮ ከሁሉ በላይ ነች። ታዲያ ወዳጄ ጥበብ መደብ የላትም። ጥበብ ስለሰው ልጅ ህይወት፣ ስለፍቅር፣ ስለተንኮል፣ ስለመሠረታዊ ስለሆነ ነገር ነው የምታነሳው። አሁን ግን ማን ይሙት በሞቴ — የካፒታሊስት ፍቅር፣ የኮሚኒስት ፍቅር የሚባል ነገር አለ? ፍቅር ፍቅር ነው?”

በዚህ ጊዜ “ኦ” ይባልና “እኚህ ሰው ቢቀሩብን ይሻላል” ተብለው ይቀራሉ።

በኢንጂነር ታደለ ብጡል ፊልም ውስጥ ከበደ ሚካኤል ከ1930 እስከ 60ዎቹ ዓመታት ታላላቅ ተግባራትን መፈጸማቸው ተወስቷል። ከ1960ዎቹ ወዲህ ግን ታላቁ የሥነጽሁፍ ሰው በችግርና በጉስቁልና መኖራቸው በቁጭት ተተርኳል። እንደ ኢንጂነር አባባል የኢትዮጵያ ምሁራንን አእምሮ ያጎለመሱ፣ በግብረ ገብነት ያነጹ፣ በሀገር ፍቅር ስሜት የገነቡ ሰው — እንደ ብዙዎቹ የኪነጥበብ እውቅ ሰዎች ተዘንግተው ኖረዋል።

 

ክቡር አቶ ከበደ ሚካኤል

ክቡር አቶ ከበደ ሚካኤል
ክቡር አቶ ከበደ ሚካኤል

ከበደ ሚካኤል ደብረ ብርሃን አካባቢ ገርሞ ገብርኤል በሚባል ሥፍራ ከእናታቸው ከወ/ሮ አፀደ ሚካኤል ተወለዱ። በተወለዱበት ቀዬ የቤተክህነት ለመማር ሲገቡ ከበደ ሚካኤል ተብለው በአያታቸው ስም ተመዘገቡ። ወ/ሮ አፀደ ከበደን የወለዱት ገና ወጣት ሳሉ በመሆኑ ከበደ እናታቸውን እማማ ወይም አይሉም — “እቴሜ” ነበር የሚሏቸው። ከበደ ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት የገቡት በአጎታቸው አቶ ሰይፈ ሚካኤልና በእናታቸው ምክክርና እርዳታ ነበር። መጀመሪያ አሊያንስ፣ ቀጥሎ ላዛሪስት ትምህርት ቤት ተማሩ። በትምህርት ችሎታቸውና እውቀታቸው ተመርጠው የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴን ልጅ ል ዑል መኮንንን እንዲያስተምሩ ለመታጨት ሁሉ ደርሰዋል። በ1929 ነው ከወ/ሮ የሺ ጋር የተጋቡት።

ከበደ ከጸሀፊነት እስከ ልዩ ባለሥልጣንና ሚኒስትር ድረስ በልዩ ልዩ መ/ቤቶች ሠርተዋል። መንግሥትን በመወከል ከቫቲካንና ከሌሎችም የውጭ ሀገር መሪዎች ጋር ለመነጋገር መብቃታቸው በፊልሙ ተመልክቷል። የኢትዮጵያን መንግሥት ወክለው ለመነጋገርና ለመፈራረም በቅተዋል።

ከትምህርት ቤት ጋር ተያይዞ አዲስ የእጅ ስራና የቴክኒክ ኮሌጅ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብቸኛ የሆነውን የአዲስ አበባ ሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት እንዲሰራ ማድረጋቸውም ተገልጧል። በውጭ ሀገር እየተዘዋወሩ ያይዋቸውን፣ ያገኙዋቸውን መጻህፍት በማንበብ የልማትና የቴክኒክ መሻሻሎችን በሀገራቸው እንዲፈጸሙ ጥረዋል።

ለዚህም “ሥልጣኔ ምንድነች?” እና “ጃፓን እንዴት ሠለጠነች?” የሚባሉ መጻህፍትን ጽፈዋል። መንግሥትም ከመጻህፍቱ ውስጥ ጠቃሚ የሆነውን ቀስሞ በተግባር እንዲያውለው መክረዋል። የጥንዳሆ እርሻን አቋቁመዋል። ኢንደስትሪዎችን በማቋቋም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበርም ተመልክቷል። አቶ ከበደ ሚካኤል ለእነዚህ ሁሉ ሥራዎቻቸው ከኢትዮጵያና ከውጭ መንግሥታት በርካታ ኒሻኖችንና ሜዳዮችን አግኝተዋል። ከሌሎች ንብረቶቻቸው ጋር ከወደሙት ተራፊዎቹ በፊልሙ ውስጥ ተደርድረው ታይተዋል።

 

ገጣሚ ከበደ ሚካኤል

“ለሁሉም ጊዜ አለው ብሏል ሰለሞን
እጠይቀው ነበር በተገናኘን
ሞት የሚሞትበት ጊዜው መች ይሆን”

— ከበደ ሚካኤል

እዚህ ውስጥ ፍልስፍና ይታየኛል። ከበደ በእነዚህ በጣም ቀለል ባሉ ግን በማይንኳኩ ተራ ቃላት ትልቅ የፍልስፍና ጥያቄ አንስተዋል። የሰለሞንን የጊዜ ተረት ፈትነውበታል። ሞት የሚሞትበትን ጊዜ ጠይቀዋል።

ከበደና መንግሥቱ ለማ በዚህ ይመሳሰሉብኛል። የሁለቱም ግጥሞች በቀላል ቃላት ትላልቅ ሀሳብን እንድናውጠነጥን ያደርጋሉ። ቃላት አይከምሩም። ወይም ቃላት ሥር አይደበቁም። ግልጽ የስነፅሁፍ ሰዎች ይመስሉኛል። እናም ከበደ እንዲህ ናቸው።

ለምን ይሆን? የሥነ ጽሁፍ መምህሮቻችን የከበደ ሚካኤልን ስም ከፍ ከፍ የማያደርጉልን?

አስፋው ዳምጤን ጠይቄያቸው ነበር።

“ወደ ኋላው ላይ የመጡትና ትምህርት ቤት የገቡት ከከበደ ሚካኤል ሥራዎች ጋር ይህን ያህል ትውውቅ ስለሌላቸው (ፋሚሊያር ስላልሆኑ) ይመስለኛል። በዚያ ላይ ወደ ኋላ ሄዶ የመመርመር ልምድ የለንም። መምህሩም እንዲያ ስለሆነ የተማረው ከየት ያመጣዋል ብለህ ነው።”

“እርስዎ ከበደ ሚካኤልን የቱጋ ይመድቧቸዋል?” ብያቸው ነበር አስፋውን።

“ከበደ ሚካኤል የስነ ጽሁፍ ሰው ናቸው። በግጥምም በስድም ይጽፋሉ። ግን በግጥም ነው በጣም የሚልቁት። እንደ ባለቅኔ ናቸው። እሳቸውም ራሳቸውን እንደ ባለቅኔ ነው የሚያዩት። የተቀሩት መጽሀፎቻቸው በሙሉ ለሳቸው እንደ ትርፍ ናቸው። በአማርኛ የወል ግጥም ውስጥ ማስተር ናቸው። እጅግ የረቀቁ ሀሳቦችን በቀላል አቀራረብ ይገልጡታል። በተረፈ ከጠቅላላ አስተዋጽኦ አንጻር ሲታይ ስለ ሥልጣኔ የጻፏቸው ኢ-ልቦለዶች ችላ አይባሉም። ታሪክና ምሳሌ፣ ታላላቅ ሰዎች፣ የእውቀት ብልጭታ — እንደ ኢጁኬተር ያስቆጥራቸዋል።”

እኚህ ታላቅ የስነጽሁፍ ሰው በኢትዮጵያ የስነጽሁፍ ታሪክ ውስጥ፣ በስነጽሁፍ የመጀመሪያውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ያገኙ ሰው ናቸው። በወቅቱ ተወዳዳሪ የነበሩትም በርካታ ሲሆኑ፣ ብላቴን ጌታ ማህተመ ሥላሴ፣ መንግሥቱ ለማ እና ፀጋዬ ገ/መድህን ይገኙበት እንደነበር የሽልማት ኮሚቴው አባል የነበሩት አስፋው ዳምጤ ገልጠውልኛል።

 

ጸሀፊ ከበደ ሚካኤል

በኢንጂነር ታደለ አገላለጽ ከበደ ሚካኤል 91 መጻህፍት ጽፈዋል። አብዛኞቹ የዚያ ጭማቂ የሆኑ ናቸው። በቁጥር 50 ቴአትሮችን ጽፈዋል። የተጻፉት በግጥምና በስድ ንባብ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ወደ ኋላ ስለቀሩ ሀገሮች የኢኮኖሚ መሻሻል፣ በተለይም ኢትዮጵያን በሚመለከት አስተያየት የሰጡባቸው መጻህፍቶቻቸው 9 ናቸው። ስለሃይማኖት መጻህፍት በመመራመር የጻፏቸው 7 የሃይማኖት መጻህፍት አሏቸው። ከተረት እስከ ታሪክ የሠፈሩባቸው 15 መጻህፍት አበርክተዋል። ሥልጣኔን በሚመለከት 4 መጻህፍት አሏቸው። ከእነዚህ በተጨማሪ በልዩ ልዩ ምክንያት ተጨናግፈው የቀሩ ከ160 በላይ መጻህፍት እንዳላቸው ይነገራል። ከበደ ሚካኤል ከ250 በላይ መጻህፍት ያላቸው መሆኑን ኢንጂነር ታደለ እንደነገሩን በፊልሙ ውስጥ ጠቅሰዋል።

መጀመሪያ በሪፖርተር ጋዜጣ ታተመ።

Subscribe to Ledesta

New writing in your inbox. English and Amharic.

Support Ledesta

Or contribute directly to sustain the publication.

Donate
አጋራ
Scroll to Top