ስብሐት ወዶ አይደለም፣
ስብሐት የማይለው፤
ወይ ትርጉም አጥቶለት፣
ወይ አግኝቶለት ነው።

‹‹ጋሽ ስብሐት ወደህ አይደለም አይደል?››
‹‹አዎ ልጄ፣ ወድጄ አይደለም!››
‹‹እስቲ ተረት አውራልኝ?››
‹‹ተረት?››
‹‹አዎ ተረት!››
‹‹እኔኮ ተረት አልችልም!››
‹‹ያው ትጽፍ የለ?››
‹‹ተረት?››
‹‹አዎ ተረት!››
‹‹ተረት እኮ አይደለም!››
‹‹እህሳ?››
‹‹ሕይወት ነው››
‹‹ሕይወት ይጻፋል እንዴ?!››
‹‹ሁሉ አይደለም እንጂ!››
‹‹ለምን ሁሉ አይጻፍም?››
‹‹ሁሉ አይገኝማ ልጄ!››
‹‹ታዲያ ጎዶሎ ሕይወት አለ?››
‹‹ለዚህ እኮ ነው ተረት ብዬ ያልኳት››
‹‹ማንን?››
‹‹ሕይወቲቷን!››
‹‹አይ ጋሽ ስብሐት!››
‹‹አይ ልጄ!››
ስብሐት ወዶ አይደለም፣
እንዲህ የሚጽፈው፤
ሰው እንዳይመረው ነው፣
እሱን እየመረረው።
ስብሐት ወዶ አይደለም፣
ድሃ ድሃ ያለው፤
የሀብትን መጋረጃ
ገልጦ ስላየው ነው።
ስብሐት ወዶ አይደለም፣
ሳቁ እናልቅስ ያለው፤
ቢፈራረቁ ነው፣
ቀን ተለሊት ሆነው።
ስብሐት ወዶ አይደለም፣
ተረት ተረት ያለው፤
ሕይወትና ተረት፣
ተምታተውበት ነው።
‹‹ጋሽ ስብሐት፣ ባለጌ ነህ አይደል?››
‹‹ሰው ብቻውን አይባልግም!››
‹‹ማለቴ የምትጽፈው እርቃንን ነው።››
‹‹ታዲያ እሱ’ኮ እውነት ነው።››
‹‹ጽሑፍህ ሁሉ እውነት ነው ማለት ነው?››
‹‹አይደለም! ውሸትም አለበት። አንዳንዴ እኮ ሰዎችን ልብስ አለብሳቸዋለሁ።››
ስብሐት ወዶ አይደለም፣
እርቃንን የጻፈው፤
አዳምና ሄዋን
ትዝ ብለውት ነው።
ስብሐት ወዶ አይደለም፣
ወሲብ ወሲብ ያለው፤
የጉድ መፈልፈያ፣
መሆኑ ገብቶት ነው።
ስብሐት ወዶ አይደለም፣
ሐቅም ውሸት ያለው፤
እንቢ ስላሉት ነው፣
አንለያይ ብለው።
‹‹ጋሽ ስብሐት፣ ሰው ምንድነው?››
‹‹የእግዜአብሔር ጽሑፍ ነው!››
‹‹እንዴት ያለ ጽሑፍ?››
‹‹ያላለቀ ጽሑፍ!››
‹‹መች የተጀመረ?››
‹‹የዛሬ 50 ዓመት››
‹‹ዕድሜህ ስንት ነው?››
‹‹ሃምሳ!››
ስብሐት ወዶ አይደለም
ገለጽ ረቀቅ ያለው
ሰውና ፍጥረቱ እያስገደዱት ነው።
ስብሐት ወዶ አይደለም
ግልጽ ልሁን ያለው
መታፈኑ ጠልቶት አየር ፍለጋ ነው።
ስብሐት ወዶ አይደለም
እንስሳ ያናገረው
አብሮ እየተኖረ ዝምታው ክብደት ነው።
‹‹ጋሽ ስብሐት ውቤ በረሓን ለምን ተውክ?››
‹‹በረሓ ብቻ ሆነብኝ።››
‹‹ውቤስ?››
‹‹ጠወለገች።››
‹‹ታዲያ ምን ተሻለህ?››
‹‹መጽሐፍ አግኝቻለሁ።››
‹‹ያኔ አታነብም ነበር?››
‹‹ያኔማ ውቤን ብቻ ነበር የማነብ።››
‹‹አሁንስ?››
‹‹መጽሐፉን አልኩህ እኮ!››
‹‹መጽሐፉ ምን ይላል?››
‹‹ውቤ የሄደችበትን አውቀዋለሁ ይላል!››
‹‹ታዲያ ነገረኽ?››
‹‹በፊት ካልጻፍክ አይሆንም አለኝ!››
‹‹ስለማን?››
‹‹ስለ ውቤ፣ ከነበረሓው››
‹‹ትገርማለህ!››
‹‹አዎ ልጄ እሱንም እየጻፍኩት ነው።››
ስብሐት ወዶ አይደለም
ላንብብ ልጻፍ ያለው
ሕይወትን አንብበህ
ጻፈው ተብሎ ነው።
ስብሐት ወዶ አይደለም
አልኮራ የሚለው
የሚኮራበት ሰው ባለማግኘቱ ነው።
‹‹ጋሽ ስብሐት ሞት መጣ!››
‹‹አይቸዋለሁ።››
‹‹ሞተህ ነበር?››
‹‹ለጥቂት!››
‹‹እንዴት ዳንክ?››
‹‹ሞትን አታለልኩት።››
‹‹ምን አድርገህ?››
‹‹አጋፋሪን ላኩበት።››
‹‹ምን ብለህ?››
‹‹ወንድ ከሆንክ ከሳቸው ግጠም አልኩት።››
‹‹እናስ?››
‹‹እየተጋጠሙ ነው።››
‹‹ለመሆኑ አጋፋሪ እንዴት እሺ አሉህ?››
‹‹እኔም የገረመኝ ይኸው ነው።››
ስብሐት ወዶ አይደለም፣
ሞትን እንቢ ያለው፤
አጋፋሪ እንዳሻው፣
አለሁ ብለውት ነው።
ስብሐት ወዶ አይደለም፣
ሙግት የገጠመው፤
የሕይወት መጨረሻን፣
ካላየሁ ብሎ ነው።
ስብሐት እባክህ የዚህን መጨረሻ ሳታውቅ
ሞትን እሺ አትበለው።
(1983 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ)
Subscribe to Ledesta
New writing in your inbox. English and Amharic.