
ከቋንቋችን ብዙ ጊዜ እምንጠቅምባት ወይም በየሄድንበት እምንሰማት አንዲት አባባል አለች “እየመጣሁ ነው” የምትል። ከሷ በላይ የምንጠቀምበት ቃል ይኖር ይሆን? ፍጹም ኢትዮጵያዊ ቃል ሳትሆን አትቀርም።
እግራችንን ካለንበት ንቅንቅ ሳናደርግ “እየመጣሁ ነው” እንላለን። መምጣት መንቀሳቀስ ነው ያለው ማነው? ሶፋ ላይ፣ ወንበር ላይ፣ አልጋ ላይ ልንሆን እንችላለን። እየመጣሁነው ከማለት ምን ይከለክለናል? ሁሉንም ጊዜ ይለየዋል፣ መሄዳችን እንደሁ አይቀር ምን ያስቸኩለናል?
ምግብ ቤት ብንሄድ፣ ምግባችን እየመጣ (እየደረሰ) መሆኑን ደጋግመን እንሰማለን። ቢርብህም ትጠብቃታለህ። መጠበቅን የመሰለ ጸጋ የለም። መጠበቅ ተስፋ ነው። ምግባችን ይመጣል። አጠገባችን የቆመችው አስተናጋጅ “ይኸው እየደረሰኮ ነው” ብትለን፣ በምን አየሽው? አንላትም። እየዋሸች አይደለም።
ሙሽሮች እየመጡ ነው። ቢዘገዩም አይቀሩም፣ “ከፈለጋችሁ እንወራረድ” ልንባል እንችላለን። ምክንያቱም በመዘግየት ምክንያት የተቋረጠ ሠርግ፣ በሰዓት ምክንያት የቀረ ስብሰባ የለም።
ይህ ውሸት አይደለም። ባህላዊ ተስፈኝነታችን ነው። እየመጣን ነን ያሉት ሙሽሮች፣ ምናልባት ከቤታቸው አልተነሱ ይሆናል። ዋናው ጉዳይ እየመጡ መሆናቸው ነው። እውነት ነዋ! ቀርተው ያውቃሉ? በፍጹም።
በዚያ ላይ በባህላችን እማናየው ውስጣችን የተጻፈ ህግ አለ።
- ሙሽሮች ደስ ባላቸው ጊዜ ይመጣሉ። ሠርጉ የሚጀመረው እነሱ በፈለጉበት ሰዓት ነው።
- ስብሰባ የሚጀምረው በሰዓቱ ሳይሆን በቂ ሰው አዳራሽ ውስጥ ተገኘ ተብሎ ሲታሰብ ብቻ ነው።
- የጀበና ቡና እንኳ እሚደርሰው ከሰሉ ብቻ ሳይሆን፣ ወሬው ሲግል እና ሞቅ ሲል ነው።
- የአዲስ አበባ ታክሲ የሚንቀሳቀሰው ሲሞላ ብቻ ነው።
- መንግሥት መብራት የሚለቀው ሲመጣ ነው።
በሀበሾች የገበታ ስርዓት፣ የጦፈ የፖለቲካ ወይም የሃይማኖት ወሬ ጣልቃ ከገባ፣ ምሳው ራት ሊሆን ይችላል።
ጊዜ በኢትዮጵያ የሁነቶች እስረኛ አይደለም። “ነፍሱ ተረጋጋ፣ ቀስ በል፣ እንዴ የት ልትደርስ ነው?…” ማለት ሞልቶ ለተትረፈረፈው የሀበሻ ሰዓት ምን ያጣድፈሃል? ማለት ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ሀበሻ ቢሮጥ እንኳ፣ ጊዜው አይንቀሳቀስም። ምን ያስሮጠዋል? ቀድሞ ነገር ጊዜውን ማን ጠርቶት ነው አቤት የሚለው።
ዛሬ 2026 በሀበሻ ዘመን አቆጣጠር 2018 ነው። ይህ ለምን ሆነ?
አሁን “አሜሪካ ውስጥ ሰዓት ይሮጣል፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይንቀረፋፋል” የሚል ሰው ሊኖር ይችላል። ዋሽንግተን ውስጥ ወፍ ዝር አይልም በሚባልበት የሥራ ሰዓት፣ ሬስቶራንቱ ግጥም ብሎ፣ ማንቺስተር እና አርሴናል ሲጫወቱ የሚመለከተውን የሀበሻ ብዛት ያየ ሰው ምን ይላል?
ኒዮርክ መካከል ቀስ ብሎ የሚሄድ ሰው ከሩቅ ከታየ፣ ያ ሰው የሀገሬ ሰው ላይሆን ይችላል ብሎ ማን ይጠረጥራል።
እሁድማ ከሆነ መርሳት ነው፣ እንኳ ሰው ጊዜም ያርፋል። ለአንድ ሰዓት ጸሎት የሶስት ሰዓት ስብከት ጠግበው የወጡ እናቶች ነጠላቸውን ፏ አድርገው መንገድ ላይ ጨረቃ ላይ እንደሚራመዱ ጠፈርተኞ ዝግ ብለው ቢሄዱ ማን ይገረማል?
ዛሬ ዓለምን የሚያራውጠው የጊዜ እጥረት ነው። ዓለም በጊዜ ቅኝ ተገዝቷል። እኛ ኢትዮጵያውን በቅኝ ያልተገዛን ብቸኛዪቱ ሀገር ብለን ብንኮራ ምን ይለናል?
ጥሩነቱ ተስፋ አለን። ተስፋ እንሰጣጣለን። እየመጣን ነው፣ ካልን እንመጣለን። “እመጣለሁ” ካልን ግን ላይሆን ይችላል። ቢሆንም ተስፋ ነው። በቃ እደውላለሁ፣ እንደዋወላለን፣ አንጠፋፋ፣ እባክህ እባክሽ እንገናኝ መባባል ተስፋ ነው። ተስፋው ላይፈጸም ቢችል እንኳ እንደዚያ መባባሉ ደስ ይላል።
“በቃ እኛ እኮ ሰው ሲሞት ብቻ መገናኘት የለብንም፣ ሁሌም መገናኘት አለብን” የሚል መፈክር፣ በየለቅሶ ቤቱ የዘመድ አዝማድ ጨዋታ ነው። አዎ ሁላችንም እንዲሁ ሳንገናኝ ሳንጠያየቅ ሞት እንዲህ ይቀድመናል እና እባካችሁ እንገናኝ ማለት የተለመደ ነው። ይህ ዓይነቱን ወሬ መተቸት አይገባም። ጥሩ ምኞት ነዋ! ይህንኑ ወሬ በሚቀጥለው ልቅሶ ላይ መነጋገር ከዚያም በሚቀጥለው፣ ከዚያም በሚቀጥለው ላይ ማውራት ምን ጉዳት አለው? ሁላችንም እኮ ከምር የምንፈልገው ነገር ነው፤ ግን አይሞላልንም። ያ አልሞላልን ያለው ነገር ግን ምን ይሆን? ጊዜ ይሆን? ወይስ እኛ ጊዜውን በሚያስፈልገን ነገር አልሞላው እያልን ይሆን?
ለማንኛውም አለመጠፋፋት ነው። መገናኘት እየመጣ ነው። እንገናኛለን!
Subscribe to Ledesta
New writing in your inbox. English and Amharic.