አጨበጨብኩልሽ፣ አጨበጨብኩብሽ
አጨብጭቤ ቀረሁ ጭብጨባዬ እንዴት ነሽ።

መጻፍ እፈለጋለሁ። አገር የሚያንቀጥቀጥ ፅሁፍ። መናገር እፈለጋለሁ አገር ጉድ የሚለው ንግግር። ብዙ ብዙ ተከታይ ያለው መሪ መሆን እፈለጋለሁ። እንኳን ለኢትዮጵያ ለአፍሪካ የሚበቃ መሪ።
እኔ ስናገር አገር በሙሉ ጸጥ ብሎ እንዲሰማኝ እፈለጋለሁ። ግን ሳስተውል አጠገቤ አንድ ክፍል ውስጥ ያሉት ሰዎች ራሳቸው ቶሎ ይሰለቻሉ። አንዳንዶቹ ቶሎ በጨረሰ ይላሉ። ለሻይ ቡና የቀጠርኳቸው እንኳ እኔ ስናገር ቀጥለው ሰለሚናገሩት እንጂ አይሰሙኝም።
አንዳንዴ አገር አንድ ጊዜ ፀጥ ብሎ ቢሰማኝ ምናለበት እላለሁ። በእርግጥ ይሔ ጭቆና ነው። ለምን እንደማልደመጥ ሳስብ ይገርመኛል።
ብዙ ሰዎች ተደመጡም አልተደመጡም ዝም ብለው ያወራሉ። መደመጥ እንደ ሎተሪ ነው። እድል ነው። ከመካከል አንዳቸው አንድ ቀን ይደመጣሉ። አሁንም የሚደመጡ ሰዎች አሉ። ሀሳብ ኖራቸውም አልኖራቸውም የመደመጥ እድል ያላቸው ወይም ሥልጣን ያበጁ ወይም ሎተሪ የወጣላቸው ሰዎች አሉ። ደንቆሮ ናቸው። አይሰሙም ማለቴ ሳይሆን ምንም ነገር አያውቁም። ግን አዳራሽ ሙሉ አሽሟጣጭ ቁጭ ብሎ ያጨበጭብላቸዋል። አንተ ምራን አንተ ተናገረን አንተ ብቻ በመድረኩ ኑርበት እያለ አንዳንዴ ቆሞ ሳይቀረ ለረጅም ጊዜ እያጨበጨበ ያወድሳቸዋል። ይህን አያለሁ።
አንድ ቀን ሹልክ ብዬ አንዱን አጨብጫቢ ጎትቼ፣ “ለመሆኑ ለምን አጨበጨብክ” ብዬ ስጠይቀው፣ “ይሄ ሰውዬኮ መሃይም ነው እንጂ ጎበዝ ነው” ብሎኛል። “ንግግር ይችላል ሀሳብ ግን የለውም” ያለኝም ሰው ገጥሞኛል።
ንግግር በመቻልና ባለ ሀሳብ (አሳቢ) በመሆን መካከል ያለውን ልዩነት መመራመር የቻለ ሰው እንዴት እንደዚያ ማጨብጨብ እንደቻለ ራሱ ሌላ አሳቢ መሆንን ይጠይቃል። “ለምን አጨበጨብክ?” ስለው “እኔ እንጃ! ያለኝን ግን አዳራሽ ይቁጥረው።
ለማንኛውም አጠገብህ ያለው ሰው ካጨበጨበ ታጨበጭባለህ። ተነስቶ ቆሞ ቪቫ ያለም ሰው ካለህ ተነስተህ ቪቫ ትላለህ። ወይ ቀንተህ፣ ወይ ንቀህ፣ ወይም የአቋም ልዩነት ኖሮህ ሊመስል ስለሚችል የግድህን ትነሳለህ።
በዚያ ላይ ደግሞ አንተ ከሰፊው ህዝብ አትበልጥም። ሰፊው ህዝብ ሲያጨበጭብ ዝም አትልም። ቢያለቅስ እንኳ አብረሀ ታለቅሳለህ። ሲዘፍን ትዘፍናለህ፣ ሲያወግዝ ታወግዛለህ። ውግዘቱ አልፎ ወረት ሲያገረሽ- “ማነሽ ባክሽ እስኪ ያን ጭበጨባዬ አቀብዪኝ…” ማለት አይቀርምና ደግሞ፣ ብዙም አትዘናጋ። ጭብጨባህን አታርቃት።
Subscribe to Ledesta
New writing in your inbox. English and Amharic.