ስልቻ ቀልቀሎ

Mengistu Lema

“… ቀልቀሎ ስልቻ፣ ስልቻ ቀልቀሎ ስልቻ ስልቻ፣ ቀልቀሎ ቀልቀሎ”

ስልቻ ባማርኛ፣ ቀልቀሎ በኦሮምኛ። ሁለቱም አንድ ናቸው። ታዲያ ምን ለያቸው? ምንም።

ይህን ለብዙ ሁኔታዎች በአዝማችነት ሊገባ የሚችል አባባል ትተውልን ያለፉት መንግሥቱ ለማ ናቸው።

እውቁ የሥነ ጽሑፍ ሰው መንግሥቱ ለማ፣ እዚህ ተወለዱ፣ እዚያ አደጉ፣ እዚያ ተመነደጉ ወዘተ. እየተባለ ስለ ሕይወት ታሪካቸው አንዳንድ ነገር ተብሏል። እሱን ዛሬ አንደግመውም። ለምን ቢሉ፤ አንድም ስልቻ ቀልቀሎ፤እንዳይሆን፤ ሁለትም ማንም ተወልዶ አድጎ ይሞታልና፤ ሦስትም ደግሞ፣ ከታወቁበት ሥራ ጋር ካልተያያዘ፣ ታሪኩ ምን ሊረባ? ያሰኛልና። እንዲህ እንዳይሆን፣ እንዲህ ቀርቧል።

የጋሽ መንግሥቱ ባለቤት ነበሩ። ወ/ሮ የሺ ወ/ቂርቆስ ይባላሉ። ስለጋሽ መንግሥቱ “እንዲህ ብለዋል” በማለት ወንደሰን በየነ ይህን ጽፎላቸዋል።

እኔ ያደግሁት በብዙ ቤተሰብ መካከል ነው። የልጅ ቤት ነው። ጫጫታ የሞላበት። ከመንግሥቱ ቤት ግን እረጭ ያለ ጸጥታ። ሆድ የሚያባባ ዝምታ፣ ጭንቅ ዋጠኝ። በዚህ ላይ ለምሳ ያቀረብኩትን ምግብ፣ አንዳንድ ቀን ብቻዬን እበላለሁ። ካልሆነም ለእራት ተመልሶ ይቀርባል። የተቀዳለትን ቡና እስኪቀዘቅዝ ድረስ የሚዘነጋበት ጊዜ ብዙ ነው። ገበታ ቀርቦ እሱ መጽሐፍ ያነባል። ባናግረውም አይመልስ። በዚህ ላይ ሌሊቱንም ከበረንዳው ላይ ከቀለሳት የማንበቢያ መከታ ውስጥ ገብቶ ይጽፋል፣ ያነባል። ደ’ሞ አንድ ነገር ከያዘ አይረሳም። በአንድ ነገር ላይ ደጋግሞ ይቆጣል። ይህ ሁሉ ሲደራረብብኝ መልመድ አልቻልኩም። ድሮም ቢሆን ሲጨንቀኝ ወደ ቤተሰቦቼ እየሄድኩ እውልና እመለስ ነበር። እያደር ሄጄ መሰንበት፣ ደ’ሞ እየታረቅን ስመለስ እንዲሁ ስወጣ ስገባ፣ ጥቂት ጊዜ አብረን ገፋን። ልጆች ከወለድንም በኋላ እንዲሁ ቀጠለ። በመጨረሻ ሁለቱን ልጆቼን ይዤ ከቤተሰቦቼ ገባሁ። እሱም ተመለሽ አላለ፣ እኔም አልፈለግሁ። የሰማንያ ውል እስከዛሬ ባይቀድም ተለያየን። ከዚያም የብቻ ኑሮ ሆነ። ባፈተተን መንገድ።

ታዲያ እንዲህ የተባለባቸው መንግሥቱ፣ ምን ብለው ይሆን? መቼም፣ አንዳንዱ የኖረውን ይጽፋል። እሚጽፈውንም የሚኖር አይጠፋም። ለማንኛውም ጋሽ መንጌ እንዲህ ጽፈዋል-

ጉድ ባይ፣ ደህና ሁኚ፤
ጥፋቱስ አይደለም፣ ካንቺ ወይም ከኔ፤
ፍቅር የመሆኑ፣ ጽድቅና ኩነኔ፤
አንቺ አንቺን መሆንሽ፣ እኔ እኔን መሆኔ።

ታዲያ ይቺን ግጥም ከባለቤታቸው አስተያየት ጋር ብናስተያያት፣ ልክክ እምትል ትመስለላች። ጋሽ መንጌ ግን፣ የግል ህይወትና ሥራቸውን ሲያገናኙባቸው እሚወዱ አይመስሉም። “የግጥም ጉባኤ” ውስጥ እንዲህ ብለዋልና።

ብቻ ላሳስባችሁ የምፈቅደው፣ ክቡር ፈቃዳችሁ ይሁንልኝና አንዲት ነገር አለችኝ። ይኸውም አንዱ መጥቶ ‘ደራሲው ይቺን መጽሐፍ ሲጽፍ፣ የጻፈው የግል ታሪኩን ነው’ ቢላችሁ፣ በሱ ሐሳብ ከመስማማታችሁ አስቀድሞ ሼክስፒርና በርናርድ ሾውን እንድታስታውሷቸው ነው። ሁለቱም ያላዩትን ያልነበሩበትን ታሪክ ነው በድራማ መልክ የጻፉት።

እሳቸው እንደሰጉት “የግል ታሪካቸውን ነው የጻፉት” ባንልም፣ ሁል ጊዜ ለያይተን ማየቱ ግን ጥሩ አይመጣም። ይህም ከሆነ፣ የሥነ ጽሑፍ ሰዎችን ታሪክ የማወቁን ፋይዳ ይቀንስብናል። ለምሣሌ፣ “መንግሥቱ ለማ፣ እንዴት እውቅ ገጣሚ ሊሆኑ ቻሉ?” ብንል፣ አስተዳደጋቸውንና አኗኗራቸውን ልናይ እንገደዳለን።

ገና በልጅነታቸው ግዕዝ ተምረዋል። ቅና ቅኔውን ዘራርፈዋል። ከደብተራ ደብተሮች ጋር ውለው አድረዋል። ኧረ ምን እሱ ብቻ፣ ተወልደዋል። ታዲያ ምነዋ ግሩም ገጣሚ አይወጣቸው? ያውም ዘመናዊ ትምህርት ጨምረውበት።

ደሞም እሺ እሱስ ይሁን፣ ታዲያ ይቺ ዘመናዊዋን አገጣጠም ከየት አመጧት? በተለይ የፍቅራፍቅሯን ብንል ደግሞ፣ ራሳቸው ከራሳቸው ሕይወት ጋር አያይዘው እንዲህ ይመልሱልናል፤

በተለይ የዘመናዊ ፍቅር ግጥሞችን ለመጻፍ መነሻ የሆነኝ፣ በልጅነት ጊዜ ዝናሽ ከምትባል የዘመዳችን ልጅ ጋር፣ ባልና ሚስት እያልን የምናጨወተው ጨዋታ፣ ያሳደረብኝ አፍላጦናዊ ፍቅር ይመስለኛል።

መቸም በመንግሥቱ አያያዝ፣ ዝናሽ ብዙ ጊዜ አብራቸው አትቆይም። ዝናሽ ስትቀር፣ ግጥሙ አይቀርም፤ ይቀጥላል። ምን ይሆን እንዲቀጥል ያደረገው? ጋሽ መንጌ፣ ወደ ሥነ ጽሑፍ ዓለም ለመግባት “በስመ አብ” ያሉባትና “ሥራ ሥራበት” ብለው የሰየሟት ግጥማቸው ይቺ ነበረች፤

ድሃ፦ እባክዎ ጌታ፣ ምፅዋት ያድርጉልኝ፣ ችግር የበዛበት፣ ፍፁም ደሀ ነኝ።

ጌታ፦ ከኪሴ ያለውን፣ የመቶ ብር ኖት፣ እስክመነዝረው፣ ታገስ ሩብ ሰዓት።

ድሃ፦ ጌታ ይቅርታዎን፣ ልድፈርዎትና፣ ስንት እንደሚሰጡኝ፣ ይንገሩኝ ለገና።

ጌታ፦ እኔስ የምስጥህ፣ አንድ ብር ነው፣ ምንዛሬ ታጣ፣ ምን ይሁን ለዚያው፤

ድሃ፦ ዘጠና ዘጠኝ ብር፣ አለኝ በምንቸት , ይዤ እመጣለሁኝ፣ አሁን በፍጥነት፤ እዚህ ይጠብቁኝ፣ እባክዎ ….. ይኸው ይዤ ከተፍ፣ አልኩኝ አሸከርዎ፤ ኖቱን ስጡኝና፣ ምላሹን ልስጥዎ።

ጌታ፦ የእኔ ብልጽግና፣ ካንተ ድህነት፤ አንድ ብር እኮ ነው፣ የሚበልጥበት፡፡ እንካ ምክርን ልስጥህ፣ ሥራ ሥራበት።

ከዚያ መንጌ፣ እንዲህ ለማለት በቁ፤

…ተማሪዎችም ብርቅ እየሆነባቸው አነበቡት። ግጥሜን ሁሉም ወደደው። ዝናው በተማሪ ቤቱ ተነዛ። እኔም ስውር የሆነ በትህትና የተሸፈነ፣ የደብተራ የካህን ኩራት ተሰማኝ። ከዚያ ወዲያ ሁልጊዜ ግጥም መጻፍ ብቻ ነበር የሚታየኝ።

የግጥሙን ብቻ ሳይሆን፣ የተውኔቱንም ዓለም ሞከርከር ያደሩጉባት ሥራቸው ይቺው ግጥም ሳትሆን አትቀርም፤

ይህን ግጥሜን በኮተቤ በምማርበት ጊዜ እንደገና ለመጀመሪያ ጊዜ በተውኔት መልክ አቅርቤዋለሁ።

ይህን የሠሩት፣ ልጅ ሆነው፣ ትምህርት ቤት እያሉ ነው። ከዚያ ሁሉ ልጅ ልቀው፣ ቀድመው በመብሰል እንዲህ ዓይነት ሥራ ለመሥራት ምን አበቃቸው?

ባባታቸው ቤት ነው ፊደል መቁጠር የጀመሩት። አባት ሲባል ደግሞ፣ የዋዛ አባት አልነበሩም። የአዲስ አበባው መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሐዲስ መምህር ነበሩ። በሌሎችም አድባራት፣ የሐዲስና የሃይማኖተ አበው ትርጓሜን እያስተማሩ፣ ብዙ ደቀ መዛሙርትን እንዳፈሩ ይነገርላቸዋል። ብዙ አድባራትንም በአለቃነት አስተዳድረዋል። መንጌ እንግዲህ የእኝህም ልጅ ናቸው።

ይህ ብቻ አይደለም። መንጌ አንዳንዴ ሾለክለክ እያሉ ጣልያኖች ዘንድ ጎራ ይሉ ነበር። በልጅ አቅማቸው ሥራ ቢጤም ሳይሞካካሩም አልቀረም። እዚያው ጣልያኖች ዘንድ፣ ቤት ለቤት ተላልከዋል። ልብሳልብስ አጣጥበዋል። በዚህ የተነሳ ከጣልያኖች ጓዳ ተዋውቀዋል። ይቺ ልምዳቸው፣ ከጽሑፋቸው እንጂ ከመሬት ጠብ አላለችም። “ፀረ -ኮሎኒያሊስት” ውስጥ-

ገብረየስ፦ ልብስ ነው የሚታጠብ። ቅድም ወዲህ ስመጣ፣ በሲኞር አርማሌዎ ቤት አልፌ ነበር። ያደፈ ልብስ ተጠራቅሞበት ኖሮ ፣ ይኽን አሸከመኝ። ታጥቦ ተተኩሶ ለነገ ካልደረሰ፣ ዱላ ትጠግባላችሁ ብሏል።

ውሂብ፦ አንድዬ ነግሬሃለሁ። የአርማሌዎን የግር ሹራብ አልችለውም-ግማቱን። የሱን ልብስ ባጠብኩ ቀን፣ እህል አይዋጥልኝም።

መንግሥቱ ጣልያኖች ዘንድ መቀጠራቸውን አባታቸው ስለደረሱባቸው፣ የድቁና ማእረግ ተሰጥቷቸው፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ተመልሰዋል። በወር ሃያ ሊሬ እየታሰበላቸው፣ ያንን የቤተስኪያን ደውል ያስነኩት ነበር። ከዚህ በኋላ ነው፣ መንጌ ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት የመጡት።

ጋሽ መንግሥቱ ሰንበት በመጣ ቁጥር ግጥም እየጻፉ፣ የሀገር ውስጥ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ። በ1940 ባህር ተሻግረው ከሎንዶን ትምህር ቤት ገቡ። “እልፍ ሲሉ…” ነውና ደግሞ፣ ከሌላ ልምድ ዘው አሉ። እናስ?


መጀመሪያ አካባቢያቸውን በዓይንም በመዳፍም አነበቡ። ካገራቸውም ጋር አገናዘቡ። እናም ያቁነጠንጣቸው ጀመር። ገና በሄዱ ባመታቸው፣ በሎንዶን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር ይመሠረት ዘንድ ከቢጤዎቻቸው ጋር ዱለታ ጀመሩ። ማህበሩም ተመሠረተ። ትንሽ ቆይተውም ፕሬዚዳንትነቱን ጠቀለሉት። ከዚያስ?

ከዚያማ፣ “ኢትዮፒስ” የሚል የብዕር ስም ለራሳቸው ሰጡ። የማህበራቸው “የላየን ክለብ” ጋዜጣ አዘጋጅ ስለነበሩም ተመቻቸው። ጽሑፉን አስነኩት። ከራሳቸውም ጋዜጣ ተሻግረው፣ በሳምንታዊው የሎንዶን ጋዜጣ ፣ ኢትዮጵያን አስመልክተው ይሉት ጀመር። በዚያ ላይ፣ ማርክሷንና ሌኒኗን ማንበብ ጀምረዋል። የዓለም እውቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችንም እንዲሁ።

አሁን እንግዲህ መንጌ፣ በደራስያን ጠበል እየተጠመቁ፣ ከሰው እየተገለሉ፣ የራሳቸውን መንገድ እየተከተሉ፣ አመፅ ቢጤ ጀመሩ። የዘመኑ መንግሥት በማይፈልገውና በማይጥመው የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ተነከሩ። በየጋዜጣውና በየማኀበሩ ደሰኮሩ። የዘር ሐረግ ጥሰው፣ ከመሳፍንት ልጅ ጋር ፍቅር ጀመሩ። በተለይ፣ ይቺን ፍቅራ ፍቅሯን “ይተው” ቢባሉ፣ እንኳን የወንዜን ልጅ፣ ሊጣ ሊጦችንም (ነጮችንም) ቢሆን አልምርም አሉ። ደሞ ፍቅር ይህን አያውቅም እያሉ መሟገት ጀመሩ። ይቺን ግጥም የገጠሟት ለዚህ ይሆን?

… ግን ፍቅር ይስባል፣ ከልጓም ከዘር፤
እሱ አገናኛቸው፣ በፈረንጅ ሀገር፤
የሚቻል ነው ለካ፣ መሆን አንድ አካል፤
ቁም ነገር የለውም፣ ባይሆን አንድ አምሳል።

በተለይ፣ የሎንዶን ቆይታቸውና “ባለ ካባና ባለዳባ” እሚለው ተውኔታቸው ቢታይ፣ ምስስሉ ጠበቅ ይላል። ተውኔቱ እሚጀምረው፣ በሎንደኑ ትዝታ ከመሆኑም ሌላ፣ የገዝሙ ገተራነት፣ ከመንጌ ባህርይ ጋር ይመሳሰላል። በወንድወሰን በየነ፣ ጥናታዊ ጽሑፍ፣ አቶ ማሞ ውድነህ እንዲህ ማለታቸው ተጠቅሷል፤

ጋሽ መንግሥቱ ቢመከር ያልተሻለው ባህርይ፣ መጨቃጨቁና እሱ ካለው ውጭ ሰማይ ምድር ቢያልፍ ሀሳቡን ቀይሮ አጉራህ ጠናኝ ማለት አይሆንለትም። ገታራ ነበር።

መንጌ በዚሁ ገተራነታቸው፣ ከዚያች ካፈቀሯት የመሳፍንት ልጅ ጋር መለያየታቸው ይነገራል። የባለካባና ባለዳባዎቹ ቢቢታና ገዝሙም እንዲሁ፦

ቢቢታ፦ አጎትዬ ስላንተ ብዙ ነገር ጠይቀውኛል።

ገዝሙ፦ ስለምን፣ ስለምኔ?

ቢቢታ፦ አጓጉል፣ ምንድነው እቴ? ድርቅና አለብህ አሉ።

ገዝሙ፦ እኮ የምን ድርቅና የኔ ፍቅር? ምን ዓይነት ድርቀት ነው? ከሳ፣ ገረጣ ነው የሚሉት? ወይስ የገቢ ምንጩ ደረቅ ነው ማለታቸው ነው?

ቢቢታ፦ እባክህ ይህ የሚያዛልቀን አይመስለኝም። ዘመዶቼ በሙሉ ዐይንሽን ላፈር ነው ያሉኝ፣ አንተን በመውደዴ።…ይህን አጓጉል ድርቅናህን እርግፍ አድርገህ ተውላቸው።

ገዝሙ፦ ብተውላቸው ምን ይሰጡኛል?

ቢቢታ፦ ቢቢታን ይሰጡሃል፤ ካምሳ ጋሻ የገጠር መሬት፣ ካስር ሺ ካሬ ሜትር የከተማ ቦታ፣ ከዘጠኝ ቪላ ጋር።

ገዝሙ፦ አታስጎምዥኝ። ድርቅናዬን ልተው አይቻለኝም። ተዋሕዶኛል። . . . አስተሳሰብህን ካልቀየርክ አለችኛ። ምረጥ አለች ከሷና ከአስተሳሰቤ። እኔነቴን መረጥኩ። እኔው ራሴን መሆን ይበልጥብኛል ብዬ፣ ለቢቢታ ነጻነቷን ሰጠኋት። ቀለበቴን መለሰችልኝ። ሄደች ተለያየን።

እዚች ጋ፣ “ጉድ ባይ ደህና ሁኚ” እምትለውን ግጥም መልሰን ብናያት፣ አሁንም ልክክ ትላለች። እንኳን ከግል ሕይወት፣ በሚሠሩት ሥራ እንኳ እየመጣች ተስማሚ መሆኗ ይገርማል። የመንጌን እና የገዝሙን የብዙ ጊዜ የብቸኝነት ህይወትም ስናስብ እንደዚያው ነው። ቢቢታን “በአላቻ ጋብቻ” ውስጥ ባናያትም፣ ስለሷ መስማታችንም ቢሆን “እንዴት ነው ነገሩ?” ያሰኛል።

ጋሽ መንግሥቱ ስድስት ዓመት ፈረንጅ ሀገር ቢቆዩም፣ ዲግሪ ይዘው አልመጡም። በዚያ ላይ ሞገደኛ ናቸው። ታዲያ እንደመጡ ማን ሥራ ይስጣቸው? ሌሎች በሥልጣን ላይ ቤት፣ በቤት ላይ ንብረት፣ በዚያ ላይ መኪና ሲታደላቸው፣ መንጌ ሥራም አላገኙ። ታዲያ መንጌ ተንኮለኛ አይደሉ፣ እንዲህ ያደርጋሉ፤

እነ ምሁር ቀፈቶ የሚንፈላሰሱበትን አውራ ጎዳና ለመረበሽ ይመስላል፣ ዶቅዶቄ ይገዛሉ። ጭስ ማውጫዋን ይቆርጣሉ። ከዚያ እንድትጮህ እንድትንጣጣ ያደርጉና፣ በየጎዳናው ያንደቀድቋታል- አዲስ አበባን በዶቅዶቄ! ወደ ኋላው ላይ የገዟት መኪናም ብትሆን ያው ነች። ዐይኗ በመጥፋቱ “ኤዲፐስ” እያሉ ይጠሯታል። አመፃ መሆኑ ነው።

መንግሥቱ ለማ፣ ካንድም አራት መሥሪያ ቤት ቢረግጡም፣ ወንበራቸውም ሆነ ኪሳቸው አላደገችም። ያቺው ነች። ከአለቆቻቸው ጋር አይግባቡም። ከጓደኞቻቸው ጋር አይስማሙም። ብቸኛ ናቸው። ከጎረቤት እንኳ አይገናኙም። የብዕር ልጃቸው ገዝሙም የሳቸው ቢጤ ነው። ወይስ እሳቸውን ነው?

ተጫነ፦ አስበው እስቲ አስበው… ስንትና ስንቴ ነግሬሃለሁ። ጠቅላላ እምነትህን ፣ አሳተሳሰብህን ብትቀይር ይህንዬ አንድ ትልቅ ቦታ ደርሰህ ነበር። እስከመቼ ድረስ ከጓደኞችህ በታች ሆነህ ትኖራለህ?

ገዝሙ፦ ምን ልሁን ተለውጨ? ማን ልሁን?

ተጫነ፦ ይህ ምን ያሳያል? የማደግ የመግነን መንፈስ የለህም ማለት ነው። የለት ጉርስ፣ ያመት ልብስ፣ የሠላም እንቅልፍ ምንድነው? ለእንስሶች ሁሉ የተሰጠ ፀጋ ነው።

ገዝሙ፦ ቢሆንም፣ ቢሆንም፣ ከእንቅልፌ ጠዋት እነሳና ፊቴን ታጥቤ፣ ጢሜን ላጭቼ፣ በመስታዉቱ ያንድ የማውቀውን ሰው ፊት አያለሁ። የማየው አያሳፍረኝም። ግንባር ለግንባር ዐይኔን ሞልቼ፣ እኔኑ ራሴን ማየት እችላለሁ።

ጋሽ መንጌም እንዲሁ ነበሩ። በትዳር ዓለም የኖሩት ለጥቂት ጊዜ ነው። ከዚያ በተረፈ ላጤ፣ ከላጤም ላጤ ነበሩ። በቤታቸው ውስጥ እሚያዩት ፊት ያው የራሳቸው ፊት ብቻ ነበር – በመስተዋት። ሌላ ማንም ዝር አይልባቸው። ወደ 2ሺ ከሚጠጉ መጻሕፍቶቻቸው በቀር፣ እሚያነጋግሩትም ነገር የለ። ብዙ ጊዜ በተለያዩ ሥራዎቻቸው “ዝምታ” እሚያሰኛቸው፣ ይህ አኗኗራቸው ሳይሆን አይቀርም። በዚህ ላይ፣ ብዙ ንባብ ሲታከልበት፣ ስለ ዝምታ እንዲፈላሰፉ ተገፋፍተው ይሆናል።

ከንቱ ነው ወዳጄ፣ መተርጐም ማተት፤
ይህ ቢሆን ይህ ሆነ፣ ስለዚህ ማለት፤
መልሳችን ዝም ሊሆን፣ ላናውቀው አንልፋ፤
ከዝም ለበለጠው፣ ራሳችን ይደፋ፤
አጥጋቢ አይደለም፣ ያው ዝም እንኳን፣
እንዲያው እንደመም፣ ቃል ፍሬ ላይሆን።

“ዝምታ ራሱ በቂ አይደለም” እሚሉት መንግሥቱ፣ እንኳን እንዲሁ፣ በድርሰትም ቢሆን፣ ደራሲው “እንዲሁ ያድርግ” ይላሉ። በ”አላቻ ጋብቻ” መግቢያቸው ላይ “ስብከቱን፣ ምክሩን፣ ትምህርቱን ለካህናተ እግዚአብሔር መተው። የደራሲ ሥራው ጥሩ ድርሰት መጻፍ ነው። መጽሐፉ ይናገር። እሱ አፉን ይያዝ።”

ይሁን እንጂ መንጌ፣ ዝም አላሉም። ሾርኒያቸው፣ ሽሙጣቸው አይጣል ነው። በአፋቸውም ቢሆን የመጣባቸው ቀን እሚቀመሱ አይደሉም። በጽሁፋቸውም እንደዚያው። በተለይ በየሥራዎቻቸው መግቢያ እሚሰነዝሯት ጠቅታ፣ የዋዛ አይደለችም። ለምሳሌ ይቺን እንይ፤

ስንኝ በሐረግ አቀነባበር ረገድ፣ የእንቆቅልሽን፣ ወይንም የአክሮባትን ጅምናስቲክ መንገድ፣ ደራሲው አልተከተለም። አጓጉል መራቀቅ፣ መመሳጠር፣ የድርሰትን መልእከት ያድፈነፍነዋል። የቅኔው አዝመራ ‘መልካም’ ነው ተብሎ የለ?

ይህን መቸም ማብራራት አያስፈልግም። ጠቅታው ግልጽ ነው። እንደፈለገው ቢመነዘር፣ “እባካችሁ እምትሉትን በቀላል ቋንቋ በሉ፣ አጉል አትራቀቁ፣ እምትሉት ይግባን” እሚል መልዕክት አያጣውም።

በሥራዎቻቸው፣ ትውልድን ከትውልድ፣ አዲሱን ከአሮጌው እያስተያዩ፣ የሰው ልጅ መልሶ በራሱ እንዲስቅ አድርገዋል። እንዳሉትም እሳቸው አፋቸውን ቢይዙም፣ ሥራቸው ግን ተናግሯል። መንጌ ለጥንቱ ትውልድ እየወገኑ፣ አባቶቻቸው እነ አለቃ ለማ ትዝ እያሏቸው፣ ያለፉበት የቤተክህነት ትምህርት እየሳባቸው፣ ዘመናዊውን ትውልድ ይወርዱበታል።

…የዘመኑ ትውልድ፣ ጦልጣላው ፈላስማ፤
ልበ ጣፊያ ሁሉ፣ ወኔው የተኛበት መንፈሰ ደካማ፤

ይሉታል። ይህን ግጥም አንብቦ “ምነው ጋሽ መንግሥቱ ምን አጠፋንና ነው?” እሚል ጠያቂ ካለም፣ በ”ጠልፎ በኪሴው” በዛብህ አማካይነት፣ እንዲህ ያብራሩታል። በዛብህ የቀድሞውን ትውልድ እያሰበ፡-

አሁን እኛ የእናንተ ልጆች ነን? ቲዮሪ አታበዙ፣ ነገር አትቀምሙ፣ ሥራችሁን ሠርታችሁ፣ አፋፍ ላይ ስትደርሱ ወኔ አልከዳችሁም። በናንተ ጊዜ፣ የነገር ሰውና የሥራ ሰው የሚባል መንታነት አልነበረም። ሰው፣ ሰው ነው። በቃ። አሳቡና ሥራ ተዋህዷችሁ ነበር። አዲስ ሥልጣኔ፣ ዘመናዊ ትምህርት በተባለው የወርቅ ሠንሠለት መች እጅ እግራችሁ ታሠረና?… የለም …በሥጋ ብቻ ነው የተወለድናችሁ።

እንግዲህ መንጌ፣ እንዲህ እየኖሩ እንዲህ ጽፈዋል። በዚህና በመሳሰሉት ባህርያቸው፣ በተለያዩ ሥራዎቻቸው፣ ተመሳሳይ ባህርይ ያላቸውን ገጸ- ባሕርያት ሊፈጥሩ ችለዋል። አቶ አቦነህ አሻግሬ ይህንኑ አይተውታል።

በተለያዩ የመንግሥቱ ለማ ተውኔቶች ውስጥ ያሉት ዐበይት ገጸ-ባሕርያት፣ በሠንሠለት ተቆራኝተው የሚገኙ ናቸው። የጠልፎ በኪሴው በዛብህ፣ ያላቻ ጋብቻው ባሕሩ፣ የጠያቂው ይግለጡ፣ የፀረ ኮሎኒያሊስቱ ካሳ እና የባለካባና ባለዳባው ገዝሙ የተለያየ ስም ይሰጣቸው እንጂ፣ በጋራ የሚጋሯቸው የአንድነት ባሕርይ አላቸው።

እነዚህን ገጸ ባሕርያት ምን አቆራኛቸው? መንግሥቱ ሳያውቁት ተጭነዋቸው ይሆን? ለማንኛውም የመንግሥቱን ሥራዎች ጨለፍለፍ አድርገን እንዳየናቸው፣ ከግል ሕይወታቸው፣ ከባህርያቸውና እምነታቸው ጋር ይቀራረባሉ። እሳቸው እንዳሉት፣ “እንደነ ሼክስፒርና በርናርድ ሾው ያልኖሩትን ጭምር” ሳይሆን፣ ያዩትና የኖሩትን ነው የጻፉት።

ይህ ጽሁፍ በመጀመሪያ በአማርኛ በ1984 (ዓ.ም) አዲስ አበባ ታትሟል።

Subscribe to Ledesta

New writing in your inbox. English and Amharic.

Support Ledesta

Or contribute directly to sustain the publication.

Donate
አጋራ
Scroll to Top