
«አንዳንዴም ከጓድ ቆምጨ አምባው አመራር ጋር ወደፊት!»
መጋቢት 1985
ቆምጨ አስተዳዳሪ ሳሉ የአንበሳ ሥዕል አሠርተው ከግርጌው «ጐጃም አንበሳ ነው» የሚል ጽሑፍ አሰፈሩበት ። ሕዝቡም በዚህ ተደስቶ ሲኖር ሳለ፣ ገበሬው ግብር በጊዜ አላስገባ ብሎ አስቸገራቸው ። ይኸኔ ቆምጨ ገበሬውን ሰብስበው ፣ «አሁን ይህን አንበሳ ላም ላድርገው?» በማለት ግዳጁን እንዲወጣ አደረጉት ይባላል ። አዎን ፣ በቆምጨ ስም የሚነገሩ በርካታ ቀልዶች አሉ ። ያለማጋነን ቆምጨ የዘመናቸው (በደርግ ዘመን) አለቃ ገብረሃና መስለዋል ። እርሳቸው ግን ይህን ክብር በመቀዳጀታቸው ደስተኛ አይደሉም ።
«ብቻ የትም ቦታ በምሄድበት ጊዜ ሰዎች ይጠቋቆሙብኛል ። በብዛት ዞረው ያዩኛል ። እኔ ሰዎቹን አላውቃቸውም ። አሁን በሄ ሰሞን እንኳ አዲስ አበባ ሄጄ ነበር ። ቅድም እንዳልኩህ ልጄን ጠይቄ ነው የመጣሁትኝ ። እዚያ አንድ ለቅሶ ነበር ። እዚያው ነው ደርሼ የመጣሁትኝ ። እና ታዲያ ያው እዚያ ፣ ያው እዚያ … ይሉኛል ። እንዴ? እኔ አልሰረቅሁ አልቀጠፍኩ ። እኔ ከሰው የተለየ ሥራ አልሠራሁ … እና ይሄ ሁሉ እኮ ሰው ያወጣልኝ ስም ነው» ይላሉ ። ደረጀ ደስታ ደብረማርቆስ ድረስ በመሄድ በስፋት አነጋግሯቸዋል ። ዝርዝሩ እነሆ ፣—
ጥያቄ ፡— ትክክለኛ ስምዎ ማን ይባላል?
ቆምጨ ፡— ቆምጨ አምባው ይልማ ። እንደዚያ ነው የምባለው ።
ጥያቄ ፡— የሕይወት ታሪክዎን ባጭሩ ቢነግሩኝ
ቆምጨ ፡— በ1933 ጎዛምን ወረዳ ውስጥ ማያ አንገታም ቀበሌ ነው የተወለድኩት ። ከዚያ እናት አባቴ ለትምህርት እንደደረስኩኝ ቤተ እየሱስ የተባለው ትምህርት ቤት አስገቡኝ ። ከዚያም ዳዊትና ድጓ ፣ ጾመ ድጓ ወጥቼ ደብረኤልያስ ቅኔ ትምህርት ቤት ገባሁኝ ። እዚያ እንደገባሁ በሽታ ገባ ። አባቴ ከዚያ አውጥቶ አገሬ መልሶ ወሰደኝ ። አያይ በሽታው ይበርዳል መልሰህ እዚያው ጨምረኝ ብለው አባቴ እምቢ አለኝ ። ከዚያ እዚያው ደብረኤልያስ ትምህርት ቤት ገባሁና የ6ኛ ክፍል ትምህርቴን አጠናቀቅሁ ። ከዚያም በነበረው ባህል መሠረት በልጅነቴ ጋብቻ መሠረትኩ ። አሁን የአሥር ልጆች አባት ነኝ ። ከዚያ የእናት ያባቴን ከብቶች ገንዲ እሚባል በሽታ ገብቶ ስለፈጃቸው በ1958 ወህኒ ፖሊስ በወታደርነት ተቀጠርኩኝ ። የአሥር አለቅነት ማዕረጌን እንደያዝኩ በ1971 የወረዳ አስተዳዳሪ ሆኜ ተሾምኩ ።
ጥያቄ ፡— እስከ 6ኛ ክፍል ብቻ ነው ማለት የተማሩት?
ቆምጨ ፡— በወረዳ አስተዳዳሪነት ከቢሁኝ ደብረወርቅ እንደተዛወርኩኝ ከ7ኛ—9ኛ ክፍል ትምህርቴን ፈጽሜ በተልእኮ (በኮርስፖንዳንስ) የ12ኛ ክፍል ትምህርቴን አጠናቅቄያለሁ ።
ጥያቄ ፡— የት የት ቦታዎች ሠርተዋል?
ቆምጨ ፡— ቢሁን ፣ እነሴ ፣ እናርጅ እናውጋ ፣ አቸፈር፣ ማቻከል ወረዳዎች፣ በወረዳ አስተዳዳሪነት ሠርቻለሁ ።
ጥያቄ ፡— የሠሯቸው ነገሮች ምን ምን ናቸው?
ቆምጨ ፡— እንግዲህ እኔ በተዘዋወርኩበት ወረዳ ሁሉ ትምህርት ቤቶች ፣ የጤና ማኅበራዊ መገልገያዎች ፣ መንገዶች ፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ያልሠራሁበትና ያልመሠረትኩበት የለም ። በተለያዩ ወረዳዎች ከ20 በላይ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ፣ ከ10 ያላነሱ ክሊኒኮች ፣ አንድ የጤና ጣቢያ ሠርቻለሁ ። የተለያዩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችንም ሠርቻለሁ ። በዚህ መስክ ለምሳሌ በሞጣ ዙሪያ አንድ ከፍተኛ የስፖርት ሜዳ አዘጋጅቼ፣ በ1977 “የኢትዮጵያ ትቅደም ዋንጫ” ውድድር እንዲደረግበት አድርጌያለሁ ። ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ብሄራዊ ዘመቻዎች ማለትም በመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ፣ በተለያዩ የጤና ነክ ዘመቻዎች ፣ በክትባትና በመሳሰሉት ሕዝቡን በማንቀሳቀስ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሳይቀር ሽልማትና እርዳታ አግኝተናል ። በእነዚህ ዘመቻዎችም ሆነ ግብር በማሰባሰብ ሂደት የተስተካከለኝ አልነበረም ። አንደኛ ነው ሁልጊዜ የምወጣው ።
ጥያቄ ፡— እነዚህን ሁሉ ሥራዎች ሲያከናውኑ ኅብረተሰቡን ለማግባባት የሚጠቀሙበት ዘዴ ምን ነበር?
ቆምጨ ፡— እንግዲህ አንደኛ የበለጠ ውጤት ለማግኘት አርሶ አደሩን አለመለያየት ነው ። ሁለተኛ ደሞ በየጊዜው ማስተማር ፣ መቀስቀስ ነው ። አብዛኛውን በማያመርትበት ቀን ፣ ሥራ በማይሠራበት ቀን ሁሉም ኃላፊ ተበትኖ እሱ ዘንድ እንዲሄድ ስለምፈልግ ሁላችንም እንሄዳለን ። በዚያ በእረፍት ቀን ለምን ቤተ ክርስቲያን አይሆንም እንዳውም እዚያ ጥሩ ነው ። ሰው አዳራሽ ውስጥ ተኮፍሶ ንግግሩ የሚጥም አይመስለውም ። ደሞ ሰው ሙቶም ከሆነ ባንድ በኩል ለቅሶው እያለ ባንድ በኩል ስለትምህርት ብናስተምረው ገለጻ ብናደርግለት ይሰማል ። ሌላው ያው ሽልማት ማበረታቻ መሳይ መስጠት ነው ።
ጥያቄ ፡— በሽልማት ማበረታታት ሲሉ እንዴት ነው? ምን ምን ምንድነው የሚሸልሙት?
ቆምጨ ፡— ለምሳሌ እኔ አንድ ዝግጅት፣ ወይም ስብሰባ እንደዚህ አዘጋጅቼ ከሆነ፣ ወንበሮች አዘጋጅና፣ ደካማ የሆነውን መጨረሻው ወንበር ላይ እንዲቀመጥ ነው የማደርገው ። በጣም ጎበዝ ፣ ኮከብ የሆነውን ደሞ ግንባር ላይ ነው እማስቀምጠው ። ግብር እሚያስገባ ፣ በጸረ ስድስት ክትባት ጥሩ ውጤት ያሳየውን «ና ያንተ ወንበር ይሄ ነው» ብዬ ከፊት አስቀምጠዋለሁ ። እንደሱ ለመቀመጥ ሲል ሌላው የግድ ይሠራል ።
ሌላ ደሞ፣ ለምሳሌ ግብር በደንብ አድርጎ ለማስገባት፣ እኔ የማሠር፣ የማስገደድ ስልት አልጠቀምም ። ይሄ ምንድነው ሜዳ ላይ እሚገደልበት መሣሪያ አለ (ክላሽ ጠብመንጃ ማለታቸው ነው) እና እሱን አስመጣና ሦስቱን አንድ ላይ በማዋቀር አውላላ ሜዳ ላይ አቆመዋለሁ ። እና ቶሎ ብሎ ሕዝቡን አስተባብሮ ግብር እሚያስገባ ካለ፣ ይህንኑ መሳሪያ ያገኛል ብዬ አስነግራለሁ ። ታዲያ ሁሉም ባንድ ጊዜ አስገብቶ ያንን መሳሪያ ለማግኘት፣ ገበሬውን ለምኖም ቢሆን እባክህ ቶሎ አምጣ፣ እኔ ልሸለምበት እያለ በማስተባበር፣ ያንን የዘመኑን ግብር ወዲያው ያስገባል ። እና መሣሪያ እንጨት ነው ምን ችግር አለ ። ሌላ ነገር የምርምር መሣሪያ እንደዚህ መስጠት ነው እንጂ እሚያቅተን፣ ሰው እሚያጠፋ ነገር መስጠት ምን ይቸግረናል ? ያንን እያነሳን እንሸልመዋለን ።
ጥያቄ ፡— ሬዲዮና ጋዜጣም ይጠቀማሉ የሚባለውስ?
ቆምጨ ፡— እንዴ እሱማ ዋናው ነው እንጂ ። የኔ ዋናው ማበረታቻ እሱ ነው ። በቀጥታ የተሠራውን ሥራ ወስጄ በሬዲዮና በጋዜጣ አስነግርለታለሁ ። ያንን ጋዜጣ ደሞ ባህርዳር ወይም ደብረማርቆስ በመውጣቱ ቶሎ አምጡ እያልኩ እንዲህ ያለ ሥራ ብትሠሩ ስማችሁ በጋዜጣ ወጣ ብዬ፣ ያንን ጋዜጣ ወስጄ ቢሮአቸው ላይ እለጥፍላቸዋለሁ ። ያኔ የእገሌ ስም በሬዲዮ ተጠርቶ በጋዜጣ ወጥቶ የኔ ቀበሌ ሊቀር ነው ወይ? እያለ እሚቆጭ ይበዛል ። እንዲያውም የኛ ለምን አይነገርም ባዩ እየበዛ ስለመጣ፣ የሠራኸውን አይቼ ትክክለኛ ሆኖ ካገኘሁት ይተላለፍልሃል እምላቸው ብዙ ነበሩ ።
ጥያቄ ፡— የእርስዎስ ስም ብዙ ጊዜ በሬዲዮ ይተላለፋል?
ቆምጨ ፡— አዎ! እንዲያውም ማስታወቂያ ሚኒስትር የቆምጨ አምባው ነው ። ሁልጊዜ እሚነገረው የሱ ነው ። እሱ ገዝቷቸዋል ። ጋዜጠኞች ሲሄዱ ይጋብዛቸዋል ። ቢራ ያጠጣቸዋል ። መስተንግዶው ከባድ ነው እያሉ ይሰድቧቸዋል ። ይህን ግን እሚያስወሩብኝ እንዴ መሥራት የተሳናቸው ሁሉ ናቸው ። ታዲያ እነሱም የት አለ ሥራ? የሠራችሁትን አሳዩና እናስተላልፍላችሁ ሲባሉ ምንም የሠሩት የላቸውም ።
ጥያቄ ፡— ሬዲዮ ሲሉ ትዝ አለኝ፣ ይሄስ ምንድነው አንድ ቀን፣ እርስዎ አወቶቡስ ውስጥ ሆነው፣ ወደክፍለ ሀገር በመንገዝ ላይ ሳሉ፣ እንዳጋጣሚ የዜና ሰዓት ነበርና፣ ዜና ሲወራ የእርስዎ ስም በመጠራቱ፣ ሹፌሩን “አቁም! አቁም!” በማለት ወደ መንገደኞቹ በመዞር “ስሙ! ስሙ! ቆምጨ አምባው ማለት እኔ ነኝ”… በማለት…?
ቆምጨ ፡— ይህ ሀሰት ነው ። ጨርሶ ካንደበቴ አልወጣም ። ለማንኛውም ጥያቄው መቅረቡ ደስ ነው ያለኝ ። ይሄ ሊወራብኝ የቻለው እንዴት መሰለህ? ገና የወረዳ አስተዳዳሪ ሆኜ ቢሁን እንደሄድኩኝ አንድም ወፍጮ በወረዳው አልነበረም ። እና ደካሞች ፣ እርጉዞች ሴቶች ድንጋይ ከድንጋይ እያፋጩ ፍዳ ያዩ ነበር ። ስለዚህ ሕዝቡን አስተባበርኩና 15 ሺ ብር እንዲያዋጣ አድርጌ ወፍጮ ቤት አስተከልኩ ። እና ያ ወፍጮ ተገዝቶ ሥራ ሲጀምር ‘በሞጣ አውራጃ የሚገኘው ወፍጮ ሥራ ጀመረ’ ተብሎ በሬዲዮ ተነገረ ። እና በሥራና በልማት የቀደምኳቸው ወረዳ አስተዳዳሪዎች ያንን አስወሩብኝ ።
ጥያቄ ፡— ምን ብለው ነው ያስወሩብዎት?
ቆምጨ ፡— እንደው ዝም ብለው ሥራ ሳይሠሩ እየተንጠራሩ ወደ ኋላ የቀሩና እኔ በልማት የቀደምኳቸው ምን ይላሉ «ወፍጮው ሥራ ጀመረ» ተብሎ በሬዲዮ ሲነገር ቆምጨ አባይ ላይ ነበረ ። ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም ይመጣ ነበረ ። እና እኔ ነኝ ቆምጨ አምባው እወቁኝ ብሎ በአወቶቡሱ ላይ ተናገረ ብለው ይህንን አስወሩ ። ያስወሩ ። እሚያሸንፍ ተግባርና ሥራ ነው ሌላ ማንም ቢያወራ አይለጠፍብኝም ። አይጻፍብኝም ። የህዝቡን ማህበራዊ ችግር ግን ካለችኝ ጭላንጭል እውቀት ጋር ከዚያ ሕዝብ ጋር በማገናኘት ችግሩን ልፈታለት ሞክሬያለሁ ። እንዴ! ወፍጮውንኮ እንዲያ ስተከለው ሕዝቡ ‘የታለ ያ ወፍጮ እሚፈጨው ሰውዬ እያለ ወፍጮ አይቶ ስለማያውቅ ‘ለመሆኑ ምን ይመስላል ምን አይነት ሰው ነው’ እስከ ማለት ሁሉ ደርሶ ነበር እኮ!
ጥያቄ ፡— ደሞ ሌሎችም አሉ ። በእርስዎ ስም የሚነገሩ ቀልዶች እንደዚህ ። ስለእነሱ እሚያውቁት ነገር አለ?
ቆምጨ ፡— እንግዲህ ከዚህ ቀደምም ቢሆን ይህ ጥያቄ ቀርቦልኝ እንደው አንድም ቀን ቀልድ እንዳልቀለድኩ ተናግሬያለሁ ። እኔ ሥራ እንጂ ቀልድ አልወድም ። ለቀልድ ጊዜ አልነበረኝም ። እንደውም በየጊዜው አሁን ድረስ እዚህ እየመጡ እሚያስቸግሩኝ አሉ ። ከተለያዩ መጽሔቶች እንደዚህ መጣን እያሉ ይጠይቁኛል ። አንዳንዶቹም እንደው ባንተ ስም መጽሐፍ ልንጽፍ ፈልገን ነበረ ። ወዲያውም ታሪክ ነው እያሉ ይጠይቁኛል ። እኔ ግን ወይዱ እኔ የናንተ መጽሔት ማሻሻጫና ማዳመቂያ አይደለሁም ። ደሞም ያላልኩትን ብትሉ እከሳለሁ እያልኩ ብዙዎችን መልሼያለሁ ።
ጥያቄ ፡— ታዲያ እነዚህ ሁሉ ቀልዶች ከምን የመነጩ ይመስልዎታል?
ቆምጨ ፡— እንግዲህ በምሳሌ ልንገርህ ። ለምሳሌ እንደዛ እንዲህ ብለው አስወሩብኝ ። የክፍለ ሀገሩ ፓርቲ ኮሚቴ ተሰብስቦ ‘በቀጥታ ወደ ሶሻሊዝም መግባት ሲቻል የብሔራዊ ዲሞክራሲ አብዮት ፕሮግራም ለምን አስፈለገ? በማለት ቆምጨን ጠየቀው ። ታዲያ ቆምጨም «እንዴ ታዲያ ለምን ሶሻሊዝምን በቀጥታ አታደርጉትም? ባለሥልጣኖቹ እናንተ አይደላችሁ? ቆምጨ ከለከላችሁ እንዴ ታዲያ?» ብሎ መለሰላቸው በማለት አስወሩብኝ ። እንግዲህ ይህ ምንን ያመለክታል፣ እኔ ደካማ፣ አላዋቂ መሆኔን በማሳየት፣ ምንም አይነት የልማት ሥራ መሥራት እንደማልችል ለማሳየት ከማሰብ የመነጨ ነው ።
ጥያቄ ፡— ለምሳሌ ቀድሞ በሞጣ አካባቢ አንድ ትልቅ የስፖርት ሜዳ ማሠራትዎን ገልጸውልኛል ። እና ያንን ሜዳ መርቀው ሲከፍቱ እንግዲህ ይህን ሜዳ የምንጠቀመው በቁጠባና በእቅድ ነው ። በሄ መሠረት በጋ በጋ ትጫወቱበታላችሁ ፤ ክረምት ክረምት ደሞ ይታረሳል… ብለዋል እሚባልም ነገር አለ ። እና…
ቆምጨ ፡— ደሞ እንዲህ አሉ? ይበሉ ምናለ! እኔ ግን ካንደበቴ አለመውጣቱን ነው እማውቀው ። ደሞ ይኸኛውን አልሰማሁትም እኔ የሰማሁት ሌላ ነበር ።
ጥያቄ ፡— ምንድነበር የሰሙት?
ቆምጨ ፡— እዎ አንደዜ ቆምጨ የስፖርት ሜዳ ሲሰራ… እንግዲህ ያኔ ሜዳው ሲሠራ ይሄ ሩሎ መንገድ ይጠቀጥቅ ነበር ። እና እኔም ቱታ ለብሼ ያንን መንገድ አስጠቀጥቅ ነበር… እና ምናሉ፣ ካሣዬ አራጋው ያኔ ወደ ሞጣ ይሄዱ ነበርና፣ እግረ መንገዳቸውን ቆምጨን አንዴ ላናግረው ብለው ና ብለው ጠሩት ። ቢሉት ያንን የስፖርት ሜዳ እየሠራ ‘አያይ እኔ አልመጣም አብዮት የማያቋርጥ እንቅስቃሴ ነው ። እና እኔም በአብዮታዊ ሥራ እንቅስቃሴ ላይ ስለሆንኩ አቋርጬ አልመጣም’ ብሏቸው እምቢ ብሎ ቀረ… እያሉ አስወሩብኝ ። እና ይሄ ምንን ያሳያል? ማእከላዊነት አለመጠበቅን ፤ ብልግናን የሚያሳይ ነው ። ግን እውነቱ እሳቸውም አልመጡም ። እኔም እንዲያ አላልኩም ።
ጥያቄ ፡— ፖለቲካ ትምህርት ቤት ገብተው ነበር እዚያም ቀልድ ቢጤ…
ቆምጨ ፡— አዎ ገብቻለሁ ። አዎ እንደውም ከዚያም አንድ ቀልድ ነበረች ። ያኔ ኢምፔሪያሊዝም እሚባል ነገር ነበረና አንዱ ተነስቶ ክፍል ውስጥ ሲያወራ ‘ብዙ አገሮች ከቅኝ አገዛዝ ነጻ በመውጣታቸው ኢምፔሪያሊዝም እርቃኑን ቀርቷል…’ ብሎ አለ ። እና ቆምጨም ብድግ ብሎ «ቁጭ በል አንተ! ውሸታም! ኢምፔሪያሊዝም እርቃኑን ሲሆን ሸንት ቤት ነው ወይ ቆሞ ያየኸው? የትእባትክ ያየኸውን ነው እምታወራው?» ብሎ ተናገረ እያሉ አውርተውብኛል ። እኔ ግን አላልኩም ።
ጥያቄ ፡— ግን የፖለቲካ ትምህርት ቤት ህይወትዎ እንዴት ነበር? ይኸው አሁን እንኳ ከቤተክርስቲያን ነው የመጡት ። ሃይማኖትና ማሌን እንዴት ያስኬዱት ነበር?
ቆምጨ ፡— አዎ እኔ መንፈሳዊነቴ መቼም ቢሆን አይለየኝም ። በዚህ የተነሳም ፖለቲካ ትምህርት ቤት ውስጥ እየጸለየ ዳዊት ተያዘበት ብለው አስወርተዋል ። እርግጥ ግን እግዜርን ልቤ መቼም አልካደውም ። ደዎም እዚያ ስገባ ማርክሲዝም ሌኒንዝምን ያራምዳል ብለው ሳይሆን በትምህርት ቢታገዝ ሕብረተሰቡን አስተባብሮ ልማትን ሊያፋጥን ይችላል ብለው ነው ።
በፖለቲካ ትምህርት ቤት ውስጥ ትዝ የሚለኝ አንድ ጊዜ ተከሰሼ ነበር ። ት/ቤቱ አካባቢ የሆነ ቡድን የልማት አስተባባሪ አድርገውኝ ነበር ። እና እኔ ልማትና ሥራ የለመድኩ ስለሆነ ካድሬዎቹ ሌዘራቸውን ፣ ወርቃቸውን አድርገው ሲንጎራደዱ እኔ ቱታ ለብሼ እሠራ ነበር ። እና ውሃ እጠልፋለሁ ፣ ድንጋይ እፈነቅላለሁ ፣ ምን እላለሁ ። እና ባንደዜ 3 ሜዳ ቆፍሬ ጨረስኩ ። ይህንን ያዩ ካድሬዎች ኡ ኡ ብለው ከሰሱኝ ። ገበሬውን አምጥታችሁብን በቁፋሮ ፈጀን ብለው አመለከቱብኝ ። አንሠራምም ብለው አመጹ ። እና እኔም አልሠራም ካሉ ይቅር እንጂ የምን ክስ ፣ የምን ጣጣ ነው ብዬ ተከራከርኩ ። ኋላ ከሠራችሁ ሥሩ ተብለው በእነሱ ተፈረደ ። እንግዲህ እማስታውሰው ይሄን ይሄን ነው ።
ጥያቄ ፡— ከቀድሞ ባለሥልጣናት ጋርስ የነበርዎት ግንኙነት ምን ይመስል ነበር ። ከፕሬዚዳንት መንግሥቱ ጋርስ እንደዚህ ተግናኝተው ያውቃሉ?
ቆምጨ ፡— ከፕሬዚዳንቱ ጋር እሚያገናኝን ነገር የለም ። እኔ አግኝቻቸውም አላውቅ ። ግን እኔ ያልተናገርኩትን ነገር እየተናገሩ ብዙ ነገር ተወርቷል ። እና እኔም እሰጋ ነበር ። ግን የደረሰኝ ነገር የለም ። ለምሳሌ አንደዜ ምናሉ ‘ባንድ ወቅት ሊቢያና ቻድ ተጣልተው ነበር ። እና ያኔ ደሞ የወቅቱ የአፍሪካ ሊቀመንበር ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ነበሩ ። እና ካሳዬ አራጋው ቆምጨን ጠርተውት ‘ቆምጨ አንተ እኮ ጎበዝ ነህ እና በአንተ አስተያየት የሊቢያና የቻድ ግጭት ምን ይመስልሃል?’ ብለው ጠየቁት እና ‘ቆምጨም … እንዴ እኔን ምን ትጠይቁኛላችሁ ሊቀመንበር መንግሥቱ ያልቻሉትን እኔ ሄጄ ላስታርቅላችሁ ነው ወይ… አለ ብለው አስወሩብኝ ። ደሞ እኔ ከባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት የለኝም ። እንዲያውም ያን ያህል ስደክም ለአውራጃ አስተዳዳሪነት ስሾም ስሜን በፍሉድ አጥፍተው ሌላ ሰው ሾመውበታል ።
ጥያቄ ፡— እና እንደው ምንም ቀልድ ወጥቶኝም አያውቅ ነው የሚሉት?
ቆምጨ ፡— እኔ በጭራሽ ። እርግጥ ምንድነው እኔ ያልኩትን በሌላ እያዞሩ እሚያወሩት ነገር አለ ። እኔን ለማጣላት ። ለምሳሌ አንደዜ ከደብረኤልያስ ድርጃ ገብርኤል እሚባል አገር ከአንድ ዋና አስተዳዳሪ ጋር እየሄድን ነበር ። በመኪና ነበር እምንሄድ ። እሳቸው የእህል ኮታ ሊገመግሙ ነው የመጡት ። እኔ ደሞ የመሠረተ ትምሕርት የምስክር ወረቀት ልሰጥ ነው ። እና ስንሄድ ከፊታችን ሦስት አህዮች እየጋለቡ ይሄዳሉ ። ይኽነዜ አስተዳዳሪው ወደኔ ዞር አሉና ቆምጨ እነዚህ አህዮች ምንድናቸው? ከቅድም ጀምሮ ከፊት ከፊታችን ይጋልባሉ? ብለው ጠየቁኝ ። እና እኔም እየውልዎት እንግዲህ እርስዎ በደንብ አድርገው እሚገመግሙ ከሆነ እኔ ሀገር እንኳን ሰው ይኸው አህያውም ነቅቷል ። እናም አቀባበል መሆኑ ነው ብዬ አልኳቸው ። እና ይቺን ወስደው አስተዳዳሪውን ‘አህያ ስለሆንክ አቀባበል እሚያደርግልህ አህያ ነው’ አለው ብለው ዞር አደረጓት ።
ጥያቄ ፡— ሌባ አይወዱም ይባላል? ለመሆኑ እንዴት እንዴት አድርገው ነበር የሚቀጡት?
ቆምጨ ፡— አዎ ሌባ አልወድም ። አንደዜ ቢሁን ወረዳ እያለሁ ሌባ በጣም በዛብኝ ። ይሰርቃሉ የተባሉትን ሁሉ ጠራሁና ጠመንጃ እያሸከምኩ ሾምኳቸው ። በሉ እንግዲህ ጠብቁ አልኩና ሁለት ሁለት ካርታ ጥይት ሰጠኋቸው ። እናንተ ታጠፋላችሁ ተብሎ በሚስጥር ተነግሮኛልና እስቲ አሁን እሚያጠፋውን እናያለን ። እናንተ ግን ጠብቁ ብዬ አደራ አልኳቸው ። ከዚያ ከብት አይሰረቅ ፤ ምን አይሰረቅ ፤ ሌባ ቀጥ አለ ። ታዲያልህ ቆየት ብሎ እንደዜ እንደው ልቤ ጠረጠረና ጋቢዝኳቸውና አረቄ እየጠጣን ‘አይ የናንተ ነገር አሁንም ትሰርቃላችሁ አሉ ። ምነ እየለማንኳችሁ? መሣሪያ መግፈፉ ማሰሩ አይረባም ያጣላል ። ስለዚህ ኧረባካችሁ?’ አልኳቸው ። በዚህ ጊዜና አንዱ ሞቅ ብሎት ነበረና ፣ አያይ አያ ቆምጨ እኛኮ አንሰርቅም ። ብንሰርቅም ከእርስዎ አገር አይደለም ከዳሞት ነው ። አለና አረፈው ። እና እኔም አለመተዋቸውን አወቅኩ ። እና እንዲያ እያደረግኩ ነው ሌባ የምይዘው ። ከማባረር ፣ ከማሰር እንዲህ ቀርቦ እያጫወቱ መያዝና መክሮ መመለሱን እመርጣለሁ ።
ጥያቄ ፡— ብዙ ጊዜ እንዲህ ገጠር ውስጥ ተዘዋውረው ሲሰሩ መቼም አስተዳዳሪ ነዎትና የቢሮዎን ሥራ ምንጊዜ ነው የሚሠሩት? ደሞ ስብሰባም ወደላይም ወደታችም ሊኖርዎት ይችላል?
ቆምጨ ፡— እኔ ብዙ ጊዜ የቢሮ ሥራ አልወድም ። 10 ቀን ቢሮ ካለሁ 20 ቀን እዳሪ ነኝ ። ስብሰባ እንኳ ስጠራ አልመጣም እያልኩ ብዙ ጊዜ እቃወማለሁ ። ዛሬ ተሰብስበን ነገ ስብሰባ ይሉኛል ። እኔ ስንት የገጠር ሥራ አለብኝ ። ከተቻለኝ አስፈቅዳለሁ ካልሆነም እምትወያዩበትን አጀንዳ በስልክ ንገሩኝ እያልኩ እጠይቃለሁ ። እና ያኔ «ስለ እህል ኮታ ፣ ስለትምህርት ፣ ስለ ምናምን ድክመት ነው…» ይሉኛል ። አያይ እኔጋ ደህና ነው የደከመውን ጠይቁ ። ከደከመው ጋር ተሰብሰቡ እያልኩ ወደ ሥራዬ እሄዳለሁ ።
ጥያቄ ፡— በአሁኑ ለውጥ ታስረው ነበር?
ቆምጨ ፡— በዚህ በለወጡ ጊዜ አዲስ አበባ ሪፖርት ሳደርግ አንድ ታጋይ ነበረ ትፈለጋለህ አለና ለ5 ቀን ታሰርኩኝ ። ከዚያ በስህተት ነው ተብዬ ተፈታሁ ። እንደገና ወዲያው ደብረማርቆስ መመደቤ ተነገረኝ ። ወደዚህ ለሥራ መጣሁ ። እዚህም እንደደረስኩ ባለሥልጣኖቹ ባህርዳር ለስብሰባ ሂዱ ስለነበረ እንደገና ለ10 ቀን ታሰርኩኝ ። ወዲያው ተፈታሁ ። ከዚያ ወዲህ የደረሰብኝ ነገር የለም ። ሥራዬን እሠራለሁ ። ከቤተሰቦቼ ጋር ነው ያለሁት ። በእውነቱ ምንም የደረሰብኝ የለም ለማለት እችላለሁ ።
ጥያቄ ፡— አሁን ያሉበት የሥራ ኃላፊነት ምንድን ነው?
ቆምጨ ፡— የጐዛሊቢን አውራጃ (የቀድሞው ደብረማርቆስ) የማህረሰቡ ጉዳይ ኤክስፐርት ሆኜ በማገልገል ላይ ነኝ ።
ጥያቄ ፡— እንዴት ነው የከተማው ኑሮ ተስማማዎት?
ቆምጨ ፡— ምንም አልል ። ወደፊት ሁኔታዎች ሲመቻቹና ተጠንተው ሲያበቁ ያኔ የበለጠ እንቀሳቀሳለሁ ብዬ አስባለሁ ።
ጥያቄ ፡— በቆምጨአምባነትዎ እንዲተላለፍልዎ የሚፈልጉት መልዕክት ይኖርዎታል?
ቆምጨ ፡— አዎ በኔ በኩል የኑሮ መሠረቱ ሥራ ነው ። እኔ የሥራ ሰው ነኝ በ15 ብር ነው ተቀጥሬ እዚህ የደረስኩት ። ቀልድ እሚባል ነገር እኔ የቀለድኩበት ጊዜ የለም ። እና ዝምብለው ነው እሚያወሩብኝ ። ስለዚህ ማንኛውም ሰው ‘የት አለ ነው ሲናገር የሰማኸው? እያለ እንደው ቢያወግዝልኝ ደስ ይለኛል ። እና እኔ አሁንም ሆነ ወደፊት አቅሜ የፈቀደውን ያህል ለመሥራት ፍላጎት ያለኝ ሰው ነኝ ። ቀልድ ምን ያደርጋል? ■
በቆምጨ አምባው ስም የሚነገሩ ቀልዶች
«አንዳንዴም ከጓድ ቆምጨ አምባው አመራር ጋር ወደፊት!»
ጋዜጠኛ ፡— ጓድ ቆምጨ አምባው ኢምፔሪያሊዝምን እንዴት ያዩታል?
ቆምጨ ፡— እናንተ እንዳሻችሁ እዩት እኔ ግን የጎሪጥ ነው እማየው
☆ ☆ ☆
አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ቆምጨን ሊጎበኟቸው ብቅ ብሎ ኖሮ «እሺ ጓድ ቆምጨ አምባው አጠቃላይ እንቅስቃሴዎ ምን ይመስላል?» በማለት ይጠይቃቸዋል ።
ቆምጨም ሲመልሱ «…እንግዲህ በዚህ በእኛ ወረዳ አብዮታዊ እንቅስቃሴው ተጧጥፏል ። በኢኮኖሚው በኩል ገበሬው ቆላውን ሰንጎ ይዞታል ። በፖለቲካው በኩል ደሞ እኔና ካድሬው ሕዝቡን ሰንገን ይዘነዋል» አሉ ይባላል ።
☆ ☆ ☆
ካድሬው ትምህርት እያስተማረ ነበር ። አብዮታዊት እናት አገራችንን የውጭ መንግሥታት እየረዱዋት ነው ። ለምሳሌ ከወዳጅ አገሮች ሶቪየት ኅብረት ፣ ኮሪያ ፣ ኩባ ፣ ቻይና እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ ። በሰብአዊው ረገድም እንግሊዝ ፣ ፈረንሳይና ጣሊያን ይገኙበታል ። ደሞም ሪሊ አሜሪካም ረድታለች… እያለ ሲያስተምር ፣
ቆምጨ የሌሎቹን እንኳ ሰምቻለሁ ። ግን ይቺ «ሪሊ» የምትባለዋን አገር ግን አላውቃትም፣ ካድሬው ትቀጥፋለህ ልበል? ብለው አፋጠጡት ይባላል ።
☆ ☆ ☆
ቆምጨ ሕዝቡን ለሥራ የሚጠሩባትና አዋጅ የሚያስነግሩባት አንዲት ጥሩንባ ነበረቻቸው ይባላል ። ታዲያ አንድ ቀን ይቺው ጥሩንባ ትጠፋለች ። ብትፈለግ አልተገኘችም ። በዚህን ጊዜ ቆምጨ ሕዝቡን ሰብስበው «የቢሆነኝ ሕዝብ ሆይ ስማ ፤ ሰሞኑን አንድ የጓድ ቆምጨ አምባው አብዮታዊ ጥሩንባ ጠፍታለች ። ስለዚህ ማንኛውም ሰው ያለችበትን ቦታ እሚያውቅ ካለ እንዲጠቁም አብዮታዊ ጥሪ ተላልፎለታል ። ካልሆነ ግን ጓድ ቆምጨ አምባው ሌላ አብዮታዊ ጥሩንባ የሚገዙ መሆናቸውን አስታውቃለሁ ።
☆ ☆ ☆
ካድሬው ሲያወራ በየንግግሩ ጣልቃ ሌኒን እንዳለው ፣ ማርክስ እንዳለው ፣ ኤንግልስ እንዳለው… ይላል ። ቆምጨም ይቺን ልብ ብለው ኖሯል ። እናም በጣም ተገረሙና ወይ ጉድ፣ እኝህ ‘አቶ እንዳለው’ እንዴት እግዜር የባረካቸው ሰው ቢሆኑ ነው እንዲህ ዓይነት ልጆች የወለዱ ። የአባትን ስም ካስጠሩ ላይቀር እንዲያ ነው እያሉ ወደሥራቸው ሄዱ ይባላል ።
☆ ☆ ☆
ቆምጨ መፈክር ይወዳሉ ይባላል ። ሆኖም ግን የሳቸው አቀራረብ ለየት ያለ ነው ።
«ሁሉም ጠላ ለመጠጣት ገብስ ያምርት!»
“ያምርት!”
«መሠረት ትምህርት የማይማር ቡዳ ነው!»
“ቡዳ ነው!”
«አንዳንዴም ከጓድ ቆምጨ አምባው አመራር ጋር ወደፊት!»
“ወደፊት!”
አስብለዋል ይባላል ።
☆ ☆ ☆
የመፈክር ነገር ከተነሳ ጓድ ካሣዬ አራጋው እንደዚ የቆምጨን አገር ሲጎበኙ ሰንብተው ይመለሳሉ ። ቆምጨም ታዲያ አለቃቸውን መሸኘት ነበረባቸው ። ደሞ አሸኛኘቱ በመፈክር ቢታጀብ ይመረጣል ። እናም ሕዝቡን እንዲህ እንዲል አዘዙ ይባላል ።
«እናቴ ኪዳነምሕረት ጓድ ካሣዬ አራጋውን በሰላም ታግባ»
ሕዝቡም «ታግባ!» እያለ ተቀበለ ።
☆ ☆ ☆
ቆምጨ ኳስ ሜዳ አሠርተው ኖሮ ሜዳው እንዳለቀ የሠፈሩን ሴት ሁሉ እበት ይዞ እንዲወጣ አዘው አስለቀለቁት ። ከዚያም ኳስ ጨዋታ ተካሄዶ ሜዳው ሲመረቅ ባደረጉት ንግግር ፡—
«እንግዲህ ዛሬ ለ24 ተጫዋቾች አንድ ኳስ አቅርበን እንድትጫወቱ ተደርጓል ። አቅማችን ሲፈቅድ ደግሞ እያንዳንዳችሁ አንድ ኳስ ይዛችሁ እንድትጫወቱ ይደረጋል» አሉ ይባላል ።
☆ ☆ ☆
ቆምጨን አንዱ አለቃቸው “መሃይም ነህ” የሚል ዘለፋ የሠፈረበት ደብዳቤ ይጽፍላቸዋል ። እርሳቸውም ለዚህ ዘለፋ ባስቸኳይ የጻፉት የእጅ ጽሁፍ ደብዳቤ ፡—
«መሃይምስ አንተ ነህ ። በእጅ መጻፍ አቅቶህ በታይፕ የምትጽፍ» አሉት ይባላል ።
☆ ☆ ☆
የመፈክር ጋጋታ የበዛበት ሰሞን ነው — ኢሠፓ ከመምጣቱ በፊት በኢሠፓአኮ ጊዜ ነው። የጊዜው መፈክርም «የኢሠፓአኮ ተልእኮ ይሳካል!» የሚል ነበር ። ታዲያ ቆምጨ አንድ ቀን ንግግር አድርገው ካበቁ በኋላ ተገቢውን መፈክር በማሰማት ሕዝቡ እንዲበተን ያደርጋሉ ። ኋላ በማግስቱ ትዝ ሲላቸው ከመፈክሮች ሁሉ «የኢሠፓአኮ ተልእኮ ይሳካል!» የምትለዋን ዘንግተዋታል ። ስለዚህ ቶሎ ብለው ሕዝብ እንዲሰበሰብ ያደርጉና በሉ ግራ እጃችሁን ወደላይ ይላሉ ። ሕዝቡ ግራ እጁን ይሰቅላል ። ታዲያ በመሃል ያቺ መዘዘኛ መፈክር አሁንም ትጠፋለች ። ቢያስቧት ፣ ቢሏት ቢሰሯት ፣ ትዝ አልላቸው ትላለች ። ይኸኔ ቆመው ተናደዱና እንዲህ የሚል መፈክር አሰሙ ይባላል —
«ሰሞኑን ከመጣው ጋር ወደፊት!»
☆ ☆ ☆
ቆምጨ የካቲት 66 ፖለቲካ ትምህርት ቤት ገብተው ለ6 ወራት የፖለቲካ ትምህርት ቀስመው ነበር ። ታዲያ በዚያችው እውቀት ሲንቀሳቀሱ ከርመው ሳለ፣ ሌሎች ካድሬዎች ለተጨማሪ የፖለቲካ ትምህርት ወደ ጀርመን መሄዳቸውን ይሰማሉ ። እንዲያ ከሆነ ታዲያ እሳቸው እናርጅ እናውጋ ውስጥ የሚቀመጡበት ምክንያት ምንድ ነው? በአስቸኳይ ማመልከቻ ማስገባት ነበረባቸው ። ማመልከቻውን ታዲያ እንዲህ ሲሉ ነው የጻፉት ይባላል —
ጓድ ካሣዬ አራጋው የ… ተጠሪ ። ከዚህ በፊት የካቲት 66 ገብቼ ለ6 ወራት የፖለቲካ ትምህርት መቅሰሜ ይታወቃል ። ስለሆነም በዚህ ባገኘሁት ትምህርት ኅብረተሰቡን ሳስተምር ቆይቼ ትምህርቱ አሁን ያለቀብኝ ስለሆነ ሌላ ተጨማሪና ብዙ ሊቆይ የሚችል ትምህርት ከወደ ጀርመን አገኝ ዘንድ ወደዚያው እንዲልኩኝ እጠይቃለሁ ።■
(እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር መጋቢት 1985 እፎይታ መጽሄት ላይ ታተመ)
Subscribe to Ledesta
New writing in your inbox. English and Amharic.