ሌባና ፖሊስ

ሌባ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይገባል። ፖሊስ ወንበሩ ላይ ተቀምጧል።

ወንድም ምን ልርዳህ?

የሰረቅኩትን እቃ ልመልስ ነበር

ከማን ነው የሰረቅከው?

አላውቅም ከማን እንደሆነ።

ታዲያ መስረቅህን እንዴት አወቅክ?

የኔ አይደለም።

የሰረቅክበትን ቦታ ታስታውሳለህ?

አላስታውስም።

ወድቆ አግኝተኸው ከሆነስ?

አይደለም።

ሰው ሰጥቶህስ ከሆነ?

አይደለም።

ታዲያ መስረቅህን በምን አወቅክ?

ይህን ነገር እፈልገው ነበር።

እና?

እሱን ብቻ አይደለም።

እሺ፤

እንዴት እንደሰረቅኩም አስታውሰለሁ።

ምን ትዝ ይልሃል?

ሰው ገድዬ ነው የሰረቅኩት።

ምን አልክ?

ሰው ገድዬ ነው።

እንግዲያውስ በግድያ ትከሰሳለህ።

የተፈለገውን እደረጋለሁ።

ማንን እንደገደልክ ታውቃለህ?

ማን እንደሆነ አላውቅም፣ ግን ሞቷል።

ታዲያ መግደልህን እንዴት አወቅክ?

መሞቱን አስታውሳለሁ።

የት እንደሆነ ታስታውሳለህ?

እዚያ ገንዘቡ ቤት።

ጤነኛ ነህ?

እንግዲህ የሰው ነፍስና እቃ እጄ ላይ ነው!

አልመለስክልኝም፣ ጤነኛ ነህ?

ጤነኛ አይደለሁም የሚል ሰው አለ እንዴ?

ከታመመ ለምን አይልም?

ሆዴን ወይም ራሴ አመመኝ ሊል ይችላል።

አንተ ሰው እብድ ነህ መሰለኝ።

አሁን ይልቅ አንድ ሌላ ነገር ትዝ አለኝ

ምን ትዝ አለህ?

የገደልኩት ሰው እብድ ሳይሆን አይቀርም!

ለምን አልክ?

ያንን ሁሉ ገንዘብ እንዴት ይዞ ይዞራል?

ገንዘብ ነው እንዴ የሰረቅከው?

አዎ በጣም ብዙ ገንዘብ።

ምን ያህል ይሆናል?

ብዙ ነው። ብለው ብለው አያልቅም!

አሁን ይዘኸዋል?

አልያዝኩትም።

ለምን?

እንዴ ብዙ ነው አልኩህኮ!

ስንት ይሆናል? አንድ ሺ፣ ሃያ፣ መቶ ሺ…?

ወደ 730ሺ ላይ ደርሼ፣ መቁጠሩ ደከመኝ

የት ነው ያለው?

እዚያው ቤት ነው!

አሁን እዚያ ማን አለ?

ማንም።

ስለ ገንዘቡ የሚያውቅ ሌላ ሰው አለ?

ነበረ፣ አሁን የለም!

ማን ነበረ?

ባለገንዘቡ ነዋ የገደልኩት!

ሌላ ያየ ሰው የለም?

ነበረ? እሱንም ገደልኩት!

ማን ነበረ?

እንዲሁ እንዳንተ ፖሊስ ነው!

ፖሊስ?

አዎ ገንዘቡን ላስረክበው ጠርቼው ነበር።

ከዚያ ምን ሆነ?

ሁለት ሆነው መጡ።

እሺ፣

አንደኛው ፖሊስ ሌሎች ፖሊሶችን እንጥራ አለ።

ከዚያስ?

ሌላኛው አይሆንም አለ።

ለምን?

ይህን ሰውዬ አስወግደን ገንዘቡን እንካፈል አለ።

ማንን? አንተን ነው?

አዎ!

ሌላኛው ፖሊስ ምን አለ?

እሱማ ሀቀኛ ነው፣ ቦታው ይታሸግ አለ።

ከዚያ ምን ሆነ?

ሌባው ፖሊስ፣ ሀቀኛውን ፖሊስ ገደለው።

አንተ እንዴት አመለጥክ?

ወደ እኔ ከመዞሩ በፊት ቀደምኩት።

ምን?

እኔን ገድሎ ገንዘቡን ሊወስድ ነበር።

አንተ ሰው ያምሃል!?

እንዴ ፖሊሱ ነው እንጂ የታመመው!

ለምን አልክ?

እውነቱን ብናገር ሊገድለኝ ፈለገ።

እንዳልከው ገንዘቡን ለመውሰድ ከሆነስ የገደለው?

እውነቱን ባልናገር ገንዘቡን የት ያውቀዋል?

እና አሁን እውነቱን እየተናገርክ ነው?

አዎ አንተም ስለ ገንዘቡ አውቀሃል!

የት ነው የምትኖረው?

ቤቴ!

እኮ ቤትህ የት ነው?

ቀበና ነው

ገንዘቡ ከቤትህ ይርቃል

ቅርብ ነው።

አድራሻውን ትሰጠኛለህ?

ምን ያደርግልሃል?

አብረን እንሄዳለን?

እኔ ከሄድኩ አድራሻው ምን ያደርግልሃል?

ወይም አንተ እዚህ ትቆያለህ?

ከዚያስ?

ገንዘቡን እናመጣዋለን?

የሀሰት አድራሻ ብሰጥህ ምን ታደርጋለህ?

ትክክለኛውን አድራሻ ለምን አትሰጠኝም?

ገንዘቡን አታመጣውማ!

ወይም አብረን ልንሄድ እንችላለን

ብገድልህስ?

ለምን?

አንተም ልትገድለኝ ትሞክራለሃ?

አልገድልህም?

ምን ዋስትና ትሰጠኛለህ?

ምን ዓይነት ዋስትና ትፈልጋለህ?

ብቻህን ከሚሆን ሌሎች ፖሊሶችም ይምጡ!

ሌሎቹማ ከመጡ ችግር ነው?

ምን ዓይነት ችግር

እዚሁ እስር ቤት ትቀራታለሃ!

ምን አለበት፣ ሰው ገድያለሁ!

የገደልከውኮ አውቀህ አይደለም!

እንዴት አወቅክ?

ራስህ በነገርከኝ መሠረት ማለቴ ነው።

ለምን አመንክ?

ለምን ልጠርጥርህ?

ፖሊስ አይደለህም?

ብሆንስ ታዲያ እውነት ስትናገር ምን ላድርግ!

እውነት መሆኑን በምን አወቅክ?

ወንጀልህን አምነህ ነዋ የመጣኸው!

ወንጀለኛ ሆንኩ እንዴ ደግሞ!

ታዲያ ሰው ገድለህ፣ ሰው ዘርፈህ!

ቢሆንም ተጠርጣሪ ነኝ እንጂ ወንጀለኛ አይደለሁም።

ራስህን ነው የጠረጠርከው።

ስለዚህ ምን ትመክረኛለህ?

በነጻ ብትሰናበትስ?

ማን ያሰናብተኛል?

እኔ?

ለምን?

እንዴ? አንተ ሰው ምንድነው ችግርህ?

ምንም ችግር የለብኝም።

ምንድነው የምትፈልገው?

ምንም አልፈልግም።

እና አሁን ምን ላድርግህ?

ምንም!

እንደዚያማ ማድረግ አልችልም!

ታዲያ አንተ ምን ይሁን ትላለህ?

በቃ ወደቤትህ ሂድ፣ ሁለተኛ እንዲህ አታድርግ?

ሰው ገድዬ?!

በቃ እንግዲያውስ እዚሁ ትበሰብሳታለህ!

እኔ ግድ የለኝም!

ገንዘቡንም ከደበቅክበት ሄደህ ታሳያለህ?

እኮ እሱን ላድርግ እያልኩ እኮ ነው!

አንተ ግን ምን ዓይነት ሰው ነህ?

ሌባ፤ ነፍሰ ገዳይ፤ ወንጀለኛ!

ለምንድነው ግን መታሰር የምትፈልገው?

አይቀርልኝማ ልሞትም እችላለሁ?

ማን ይገድልሃል?

ገንዘቡን የምትፈልጉ ሰዎች?

በቃ እንዳልከው ሌሎች ፖሊሶች ይምጡ?

እሺ!

እኔና አንድ ፖሊስ እጨምራለሁ?

ሁለታችሁ ብቻ?

ስንት ፖሊስ ነው የምትፈልገው?

ቢያንስ አምስት ስድስት መሆን አለባችሁ!

እንዴ ይሄ ሁሉ ፖሊስማ አይንጋጋም?

ገንዘቡኮ ብዙ ነው? ማን ይሸከማል?

700ሺ ምናምን ነው አላልከኝም እንዴ?

እኮ፣ አንዱ ሻንጣ ውስጥ ነዋ። ሻንጣዎቹኮ ብዙ ናቸው?

ምን አልከኝ?

ሻንጣዎቹኮ ብዙ ናቸው?

ስንት ይሆናሉ?

እኔ እንጃ ላይ አንድ ስድሰት… ታች ሶስት… እዚጋ….

በቃ በቃ። ባንክ ቤት ነው እንዴ የዘረፍከው?

አይደለም፣ መኖሪያ ቤት ነው።

ይሄ ሁሉ ገንዘብ?

አዎ ሰውየው ዶላር ይመንዘር ምን፣ አላውቅም….

ይሄማ ከሚሊዮን ብር በላይ ሊሆን ነው

አዎ ብዙ ሚሊዮኖች ይሆናል?

እኔ እምልህ ምሳ በልተሃል?

አልበላሁም?

ምን ላምጣልህ?

የፈለግከውን አምጣልኝ!

እንዲያውም ለምን ወጥተን አብረን በልተን አንመጣም?

እንዴ እስረኛ አይደለሁም እንዴ?

ሰውዬ ገና አልታሰርክም ማን አሰረህ?

እንዴ ፖሊስ ጣቢያ አይደለሁም እንዴ?

ብትሆንስ ጣቢያው እስር ቤት አይደለም።

ውጭማ አልወጣም?

እንዴ ለምን?

ነገርኩህኮ ይገድሉኛል

እኔ እጠብቅሃለሁ?

የምፈራው አንተን መስሎኝ?

በል ስማ፣ አሁን ድምጽህን ዝቅ አድርገህ እናውራ?

እሺ ምን ላውራ?

ስማ ይሄ ገንዘብ በጣም በጣም ብዙ ነው…

ቢሆንስ?

ሌላ ሰው ከሚበላው እኛ ለምን አንካፈለውም?

እኔ ገንዘቡን አልፈግልም?

እሺ ታዲያ እኔ ብወስደው ችግርህ ምንድነው?

ውሰደው እኔ ምን ቸገረኝ?

አድራሻውን ንገረኛ?

ግን ብነግርህ ታምነኛለህ?

ምን ምርጫ አለኝ ለምንስ እጠረጥርሃለሁ?

ለነገሩ እኔም ካላየሁት አላውቀውም?

ቅድም አውቀዋለሁ ብለህ አልነበረም?

መስሎኝ ነበር ግን የግድ ማየት አለብኝ።

አሁን የሆነ ቦታ ደርሼ ብመጣ ለሰው ትነግራለህ?

ከጠየቁኝ ምን አደርጋለሁ?

ማን ይጠይቅሃል?

ፖሊሶቹ ናቸዋ?

ዝም ማለት አትችልም?

ይደበድቡኛላ!

ምን አይነት ጣጣ ነው ባካችሁ?

በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው።

ደግሞ እንደሱ ትላለህ እንዴ?

ተቸግረህ እያየሁ፣ ምን ልበል?

አንተ ግን አልተቸገርክም?

አሁንማ ተገላግዬ!

እንዴት?

አንተ አለህልኛ?

ለምን?

ማን ይነካኛል?

እንዴት?

እንኳን ሌላ ሰው፣ አንተም አትነካኝም።

አሁንማ እንዴት አድርጌ?

አንተ ፖሊስ ነህ ገንዘቡ ለምን አይቀርብህም?

እንዴ ለምን? የምሰራው ለሱ መስሎኝ!

አያይ ገና ሳታገኘው ተሰቃየህ ብዬ ነው?

ላግኘው እንጂ ስቃዩ መቸ ከፋ ብለህ ነው?

አግብተሃል?

እንዴ እንዴ እንዴ እግዜር ይስጥህ!

ምነው?

እንዲያውም ሚስቴን ደውዬ አማክራታለሁ?

ልጅ አለህ?

የለኝም። ሚስቴ ጥሩ ዘዴ አታጣም።

በል ደውልላት።

ግን ምን ብዬ እነግራታለሁ?

ደውልና ለኔ ስጠኝ እኔ እነግራታለሁ?

ምን ብለህ?

ከቻልክ ንገራት፣ ካልቻልክ እኔ አደርገዋለሁ።

ምን ልትላት ነው?

ምንቸገረህ ወይ አንተ ሞክር ወይ አገናኘኝ?

ወይ እግዚአብሔር ደግሞ ሚስቴን እዚህ ውስጥ

እዚህ ውስጥ ምን?

እዚህ ጣጣ ውስጥ ልከታት ነው?

አዎ! ገንዘብ እኮ ጣጣ ነው።

በጣም ቆሻሻ ነገር ነው።

ታዲያ ለምን አይቀርብህም?

ወድጄ መስሎህ ነው?

ማን አስገደደህ?

ኑሮ ነዋ! ሚስቴ… ደኸዋ እናቴ…

እናትህ የት ናቸው?

ባላገር ናት፣ ገጠር ውስጥ።

ገንዘብ ብታገኝ ምን ታደርግላቸዋለህ?

እዚህ አመጣት ነበር!

ከዚያስ?

እንዴ? ምን ከዚያስ አለው?

መጥተው ምን ይሆናሉ?

ተንቀባራ ትኖራለቻ!

ምን ያህል ይበቃቸዋል ለመንቀባረር?

ተንቀባርሬ አላውቅ በምን አውቀዋለሁ?

ታዲያ ለምን እርግጠኛ ሆንክ?

ገንዘብ ነዋ?

ገንዘብ ሳይኖርህ እንዴት አወቅክ?

ገንዘብ እኮ ከመጣ በኋላ የምታውቀው ነገር ነው።

እሱስ ልክ ነው።

ገንዘብ ይለውጣል።

በደንብ እንጂ፣ ገና ሳይመጣ እንኳ ሲለውጥህ አየሁ።

ምን አልክ?

ለሚስትህ ደውልላት!

ደውየ ምን እላታለሁ አልኩህኮ

ለእኔ ትሰጠኛለህ።

አንተስ ምን ትላታለህ?

ካገኘኋት በኋላ ነው የማውቀው?

ጤነኛ ነህ?

ሰውዬ ጤነነቴን ነው፣ ገንዘቡን ነው የምትፈልገው?


ፖሊሱ ይደውላል። ሰናይት ታነሳለች።

ሀሎ

አቤት?

ማሬ እንደምን ዋልሽ

አለሁልህ እንዴት ነህ?

የት ነው ያለሽው?

ቤት ነኝ። ምነው?

ሰው አብሮሽ አለ?

እንዴ ቢኖርስ? አለ ልልህ ነው!

አትቀልጂ በናትሽ፣ አንድ ነገር ልንገርሽ ነው?

ማንም የለም፣ ንገረኝ።

ይኸውልሽ አንድ ሰው አገናኝሻለሁ?

የምን ሰው?

ምንም ነገር አትጠይቂ፣ ጊዜ የለም!

እንዴ ምንድነው ነገሩ፣ ከምርህ ነው?

አዎ ጊዜ የለም፣ ቶሎ ቶሎ ማድረግ አለብን?

ሰውየው ስትል?

እየውልሽ የሚልሽን ሁሉ እሺ በዪው

እንዴ እኔ የምልህ…

ለኛው ጥቅም ነው፣ በጣም ትልቅ ጥቅም

እንዴ ቆይ አስረዳኝ እንጂ

ሌባው ስልኩን ይቀበላል።

ሀሎ!

ሀሎ አቤት!

ማሬ ነሽ?

ማሬ አይደለም፣ ስሜ ሰናይት ነው።

አይ ባለቤትሽ “ማሬ” ሲልሽ ሰምቼ ነው።

ሆሆ እሺ ማን ልበል?

ባለገንዘቡ ነኝ።

የምን ገንዘብ?

አይተሽው የማታውቂው ገንዘብ?

አልገባኝም።

አሁን እንዲገባሽ ነው የደወልኩት።

አሁንም አልገባኝም።

ካልነገርኩሽ እንዴት ይገባሻል?

ይሺ ይንገሩኝ!

አንተ በዪኝ ግድ የለም።

እሺ ንገረኝ!

ለሁለታችሁም የሚበቃ ብዙ ገንዘብ አለ።

የት ነው ያለው?

የሆነ ቦታ?

ኡኡቴ የትኛው ባንክ ነው

እየቀልድኩ አይደለም።

አቤት?

ካሁን በኋላ ብትቀልጂ እዘገዋለሁ?

ቶሎ ንገረኛ!

ገንዘብ ለማግኘት ትዕግስት የለሽም?

ደግሞ ገንዘብ በትዕግስት ይገኛል እንዴ?

ነግሬሻለሁ፣ የመጨረሻ እድል ነው፣ እዘገዋለሁ።

እሺ አደምጣለሁ!

በአስር ደቂቃ ባልሽ ሥራ ቦታ ፈጥነሽ ድረሺ!

አቤት?

ጨርሻለሁ! ባልሽን አናግሪው።

ፖሊሱ ስልኩን መልሶ ይቀበላል።

ሀሎ ማሬ

እንዴ ምንድነው ነገሩ?

በቃ አሁኑ ሮጠሽ ነይ

እንዴ ቆይ እንጂ?

ስሚ ጊዜ የለም ቶሎ በይ!

መጥቼ ምንድነው የማደርገው?

አትጠይቂ ዝምብለሽ ነይ?

እኔምልህ…?

ቻው ቻው በቃ ቻው!!


ስልኩን ይዘጋል።

ዘጋህባት እንዴ

ታዲያ ምን ልበላት?

እና ትመጣለች?

እሱን አውቀህ አይደል እንዴ?

ምኑን?

ነይ ያልካት?

እሱስ አዎ፣ ገንዘብ ጠርቶት ማን ዝም ይላል?

ከመጣች በኋላ ምን አስብክ?

አብረን እንሄዳለን።

የት?

ቤታችሁ!

እኛ ቤት?

አዎ!

ለምን?

ከዚህ አይሻልህም?

እሱስ ይሻላል፣ በጣም።

ቤታችሁ ሩቅ ነው?

አስር ደቂቃ ያልከው ሳታውቅ ነው?

አላውቅም። አዛዥ በራሱ እንጂ በታዛዡ ጊዜ አያዝም።

እና አዛዥ ነህ ማለት ነው?

ካንተ አልፌ ሚስትህን ላዝ መስሎኝ?

ስድቡ ግን ቢቀርብህስ?

አንተ ገንዘቡ ቢቀርብህ አይሻልም?

ካልተሰደብኩ ማግኘት አልችልም?

ተሰድበህም ባገኘኸው።

ምን አልክ?

ተሰድበህም ባገኘኸው?

ላላገኘው እችላለሁ ማለት ነው?

እኔ ምን አውቃለሁ።

እንዴት?

እኔ፣ አንተ፣ ሚስትህ፣ ሶስት ሆንኮ።

ያልከው ገንዘብ ለሀገሩ ሁሉ አይበቃም?

ብታገኘው ለሀገር ሁሉ ታካፍለዋለህ?

አንተ ሰው በጣም ተጫዋች ነህ።

ጥያቄው ሲከብድህ ጨዋታ አደረግከው?

አልከበደኝም።

ታዲያ ለምን አልመለስክም?

እጄ ላይ በሌለ ገንዘብ ምን ልመልስ?

እጅህ ላይ በሌለ ገንዘብ ሚስትህን ጠርተህ?

አንተ ነህ የጠራኻት እኔ አይደለሁም።

እርግጠኛ ነህ?

ታዲያ ምን ልትል ነው?

ያለውን ሁሉ እሺ በዪው አላልክም?

እና ብልስ?

ትዕዛዙኮ እሱ ነው።

እና?

ሚስትህ እየመጣች ነው።

እና?

ከዚያ ወደ ቤታችሁ እንሄዳለን።

ከዚያስ?

ከዚያ ደግሞ የሚሆነውን እናያለን።

ሌላ ነገር ብትል ግን ነግሬሃለሁ?

ምን ታደርገኛለህ?

በጣም አስቸጋሪ ሰው ነህ?

ምርጫው ያንተ ነው፣ ላልሄድም እችላለሁ።

ሚስቴንማ እዚህ ድረስ ጠርተህ…?

‘ጠርተህ’ አትበለኝ ብዬሃለሁ።

ግድ የለም፣ ዋናው መሄድህ ነው?

እንዲያውም ሳስበው ባልሄድ ጥሩ ነው።

እንዴ! አሁንማ አበዛኸው።

እንዴት?

ሚስቴ እየመጣች ነዋ!

ብትመጣስ ታዲያ ሀሳቤን መቀየር አልችልም?

እንዲህ የሚያደርግህ ግን ምንድነው?

ገንዘብ ነው።

ቅድም አልፈልገውም ስትል አልነበር?

አሁንም አልፈልገውም።

ታዲያ ሀሳብህን ምን ያስቀይረሃል?

ቤትህ ሄጄ፣ የበለጠው እስር ቤት ውስጥ እገባለኋ!

ለምን ትታሰራለህ፣ እዚያማ ይመችሃል።

ለምን ይመቸኛል?

አንደኛ ጥሩ እንክብካቤ ታገኛለህ?

ምን ታደርጉልኛላችሁ?

የፈለግከውን።

ወይስ እናንተ የፈለጋችሁትን?

አንተ ሰው በጠበጥከኝ?

ምን አልከኝ?

አያይ የፈለግከውን እናደርግልሃለን።

ባለቤትህ እሷ ናት?

የታለች?

ያቺ ሴት እሷ እንደሆነች ብዬ ነው?

አዎ ናት እንዴት አወቅካት?

ስትቅበዘበዝ ታስታውቃለች?

አንዴ ላናግራት መጣሁ

ሄድ ግድለም እዚሁ ነኝ።


ሌባው ወደ ሰናይት ይቀርባል።

ተዋወቃት ባለቤቴ ናት ሰናይት ትባላለች?

ሰላም ማሬ!

ሰናይት ናት አልኩህ እኮ።

ማሬ ብዬ ብጠራት ምን አለበት?

ግድ የለም እንደፈለገው ይጥራኝ። ሰላም!

እንዴት ነሽ?

አለን፣ አሁንኮ ሁሉንም ነገር ማሬ ነገረኝ

እንዴ እሱም ‘ማሬ’ ነው እንዴ?

አዎ “ማሬ” ነው የምንባባለው?

ወይጉድ የኮሶ ቤት ሰው ማሬ ማሬ ሲባል…

ምን አልክ??

አያይ እንግዲያውስ ትቸዋለሁ፣ማነሽ ሠናይት!

ምኑን የው የተውከው?

ማሬ ማለቱን?!

እንደፈለግክ፣ አሁን ምን እናድርግ?

ባልሽ እንደነገረሽ ወደቤታችሁ እንሂድ

እሺ እንሂድ ተነስ።

በምንድነው የመጣሽው?

በባጃጅ ነው። እኛ ግን በታክሲ መሄድ እንችላለን?

ግድ የለም እንዲያውም በእግር እንሂድ?

ቀጥታ ወደ ቤት ነው የምንሄደው?

አዎ ለባልሽ ነግሬዋለሁ።

አዎ ነግሮኛል።

እንዴ የታል ባልሽ?

ያው ከኋላችን አለ።

ለምን?

እኔ ከኋላችሁ ልከተላችሁ፣ ሰው እንዳያየን አለ።

ጥሩ አድርጓል?

አዎ ይሻላል።

ከተጋባችሁ ቆያችሁ?

ሰባት ዓመት ሆኖናል።

አንቺ ሥራ አለሽ?

የለኝም።

ታዲያ እንዴት ትኖሪያለሽ?

ባሌ ይሰራል፣ እኔም አንዳንድ ነገር እሞክራለሁ።

ምን ትሞክሪያለሽ?

ምን እማልሞክረው ነገር አለ?

ልጅ ለምን አልወለዳችሁም?

እምቢ አለኝ።

ወይስ እምቢ አላችሁ?

ምን አይነት ጥያቄ ነው?

እንዴት?

ባንዲት ሰከንድ ስንት ነገር ጠየቅከኝ?

ጥያቄ ላቁም?

የምትናገረው ከሌለህ?

ለመጫወትኮ ብዬ ነው።

ሌላ ጨዋታ የለህም?

ገንዘብ ትወጂያለሽ?

ገንዘብ የሚጠላ ሰው አለ እንዴ?

እኔ አልወድም!

ባሌ በጣም ያመነህ ይመስላል።

አንቺ ተጠራጠርሽ?

መች ለማሰብ ጊዜ ሰጣችሁኝ?

ምን ያህል ጊዜ ያስፈልግሻል?

ለምኑ?

ለማመን!

እንዴ እኔኮ ምንም ነገር አላውቅም።

ምን ማወቅ ፈለግክሽ?

ነገሩ ተረት ይመስላል።

ለምን እንደሱ አልሽ?

የማይመስል ነገር ነዋ!

ምኑ?

የተባለው በሙሉ?

ምን ተባለ?

እንዴ! እኔ ምን አውቃለሁ?

ምኑን ነው የማታውቂው?

ያላችሁትን ሁሉ ነዋ?

ምን አልን?

የሆነ ቦታ፣ የሆነ ብዙ ገንዘብ አለ…

እና?

ከዚያ ሄደን እናመጣዋለን

ከዚያስ?

ከዚያማ ምን አውቃለሁ?

ገንዘቡን ካመጣን በኋላ ምን የምናደርግ ይመስልሻል?

እኔ ምን አውቃለሁ?

እንዴት አታውቂም?

እንዴት አውቃለሁ?

ሎተሪ ቢወጣልሽ ምን ታደርጊያለሽ?

እኔ ሎተሪ ቆርጨ አላውቅም

ለምን አልቆረጥሽም

አይወጣልኝማ

ለምን አይወጣልሽም?

እንዴ የገዛ ሰው ሁሉ ይወጣለታል እንዴ?

ያልገዛ ሰውስ ይወጣለታል?

ያልገዛማ ለምን ይወጣለታል?

ታዲያ ቢወጣልሽ አይሻልም?

ወይኔ…! አድክም ነገር ነህ።

እና የተባለውን ገንዘብ አላምንም እያልሽ ነው?

‘አላውቅም’ ነው ያልኩት።

ባለቤትሽ ግን ያውቅ ይመስልሻል?

እሱማ አምኖሃል አልኩህኮ

ስለዚህ እሱ አመነ፣ አንቺ ተጠራጠርሽ?

እንደሱ መሰለኝ።

ከዚህ ሁሉ ቢቀርስ?

ምኑ?

ገንዘቡ ነዋ!

እንዴ እዚህ ክተደረሰ በኋላ?

አዎ እንዲያውም እኔ እዚያው እስር ቤት ልመለስ?

እንዴ እንደሱማ አይሆንም።

ለምን አይሆንም?

ምንድነው እየቀለድክ ነው?

ምን አስቀለደኝ?

እኔ እኮ ስቀልድ ነው።

ምኑን ነው የቀለድሽው?

አላምንህም ያልኩት?

አሁን አመንሽኝ?

ወይኔ በናትህ…ባሌን አታበሳጨው።

ለምን ይበሳጫል?

ይህን ሁሉ አድርጎ፣ እዚህ ደርሶ?

ታዲያ አንቺ ነሻ!

እኔማ ምን አደርጋለሁ?

እንዲያውም ግድ የለም ቤት እንድረስ።

ከዚያ ምን አሰብክ?

አንቺን ትተን እኔና ባልሽ ብቻ እንጨርሰዋለን።

አሁንማ እኔም አለሁበት። ወዴት ወዴት?

እንዴ አሁን አላምንም ብለሽ አልነበር እንዴ?

ታዲያ ብልስ?

እየተጠራጠርሽ እንዴት ይሆናል?

እኔኮ ነገሩን ነው እንጂ፣ ብሩን አልጠረጥረውም።

አሃሃሃሃ በጣም ቀልደኛ ነሽ።

እንዴ ታዲያ ምን ልበል?

አሁን ያሁሉ ገንዘብ ቢደርስሽ፣ ምንታደርጊያዋለሽ?

ይምጣና ይቸግረኝ።

ግን አደጋው አይታይሽም?

የምኑ?

የህጉ ነዋ?

ህጉ ምንያደርገኛል?

ባልሽ ፖሊስ ነው፣ አንቺም ተባባሪ ነሽ

ብንሆንስ ታዲያ?

ነገ ብትያዙ ምን ትያለሽ?

ለምን እንያዛለን?

የገባሽበትን አታውቂውም?

እኔ ምንም ውስጥ አልገባሁም?

መግባትም አትፈልጊም?

አልፈልግም?

እንግዲያውስ እንዳልኩት እኔና ባልሽ ብቻ እንጨርሰዋለን

እንዴ እናንተ ህግ አትፈሩም ማለት ነው?

እኔ አልፈራም፣ የባልሽን አላውቅም።

እሱማ እስከዛሬ ህጉ ህጉ እያለ ድሃ አድርጎ አስቀረን።

ምን ማድረግ ነበረበት?

ዝም ብሎ እኔ የህዝብ አገልጋይ ነኝ የሚለው ነገር አለው።

ከሌቦች አይተባበርም፣ ጉቦ አይቀበልም?

በፍጹም ባሌ በጣም ንጹህና ሀቀኛ ሰው ነው።

ያን ያህል ታምኚዋለሽ ማለት ነው?

አዎ ኑሯችንን አውቀዋለሁ፤ ሳይበላ የሚውልበት ቀን አለ

ደመወዝ አለው አይደለም እንዴ?

ደመወዝ? አታስቀኝ ባክህ። ፖሊስ ደመወዝ የለውም።

ግን እኮ ሰው አያምናቸውም?

ሰውማ ፖሊስ ከሌባ እንዲጠብቀው ነው እንጂ ፖሊስ ባይበላም ግድ የለውም

ፖሊሶች የሚጠሉ ይመስልሻል?

አዎና ምን ጥያቄ አለው፣

አዎ ልክ ነሽ ሰው ሲሰርቁት እንጂ ሲሰርቅ ፖሊስ እንዲያገኘው አይፈልግም

አንተ ግን ገንዘቡን ሰርቀህ ነው?

አዎ

እና ሰርቀህ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄድክ?

አዎ?

ለምን?

ገንዘቡ ብዙ ነው አልኩሽ እኮ?

ትንሽ ገንዘብ ቢሆን አትሄድም ነበር?

ትንሽ ገንዘብማ ቢሆን አልሰርቅም ነበር።

የሆንክ ጠማማ እና ምታስቅ ነገር ነህ

ባልሽን ግን እዚህ ውስጥ ሲገባ ለምን ዝም አልሽው?

እኔም ገርሞኛል። በጣም አስደንግጦኛል።

ለምን አስደነገጠሽ?

አንደኛ ከመርሁ ውጭ ነው

ሁለተኛ

እኔን እንጃ ከዚህ እንዴት አመልጣለሁ ብሎ እንዳሰበ አላውቅም

እዚህ ውስጥ ለምን የገባ ይመስልሻል?

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለወጠ ይመስለኛል?

ምን ለወጠው?

የሰፈሩም ቤተሰቡም ሁሉ በአሽሙር ይሰድቡታል

ምን እያሉ?

ሀገር ውስጥ ላለው ሁሉ ነገር ተጠያቂ ያደርጉታል

ለምሳሌ?

ለምሳሌ ቤት የፈረሰ እንደሆነ የድሃ ቤት እያፈረሳችሁ ይላሉ

ሌላስ?

ጉቦ ሲበዛ እናንተ ጉቦ እየበላችሁ ከሌባ እየተባበራችሁ ይላሉ?

እና በዚህ ምክንያት ነው የምትዪኝ

እሱ ብቻ አይደለም። የናቱ መታመም፣ የኔ መነጫነጭ፣ የኑሮ መወደድ ብዙ ነው።

ይገርማል መጣሁ፣ አንዴ ሽንት ቤት ደርሼ?


ሌባው ራቅ ይላል። ሰናይት ወደ ባሏ ዞር ትላለች።

እንዴ ማሬ! ሰውየው የት ሄደ?

ሽንት ቤት ነው። ተረጋጋ!

ቆየ እዚያ ውስጥ?

እንደመጣን ነው የገባው። እስካሁን አልወጣም

እንዴ ዝም ትያለሽ እንዴ?

እንዴ ታዲያ ምን ልበለው፣ ሽንት ቤት እኮ ነው

ማለቴ በጣም ከቆየ ብዬ ነው?

የት ይሄዳል ብለህ ነው፣ መስኮት የለው።

አንቺ እዚጋ የተቀመጥሽው በሩ እንዲታይሽ ብለሽ ነው?

አቤት አንተ፣ ሊሆን ይችላል። እኔ ግን እንደሱ አላሰብኩም።

መንገድ ላይ አወራችሁ?

ትንሽ አወራን አዎ፣ ግን ግራ ያጋባል።

ምኑ ነው ግራ የገባሽ?

እኔ እንጃ! አለ አይደል…

አላመንሽውም?

እሱማ ምን ምርጫ አለ?

እንዴት?

አላምንም ብሎ ከመቅለጥ፣ መሞኘት ይሻላል።

እሱን ብዬ ነው እኮ እኔም፣ደግሞስ ማን ያውቃል?

አንተ ግን የት አገኘኸው?

ጣቢያችን ድረስ ሰተት ብሎ መጣ።

እና ምን አለ?

ሰው ገድያለሁ፣ እጅ ልሰጥ ነው አለ።

ሰው ገድሏል እንዴ?

አለ እንግዲህ፣ ይላል።

ይሄማ ችግር ነው?

አዎ ችግር መሆኑ አይቀርም።

ታዲያ የገንዘቡ ነገር ከየት መጣ?

እዚያ የገደልኩበት ቤት ውስጥ ብዙ ገንዘብ አለ ይላል?

ብዙ ሲል ስንት ነው?

ማን ያውቃል፣ በብዙ ሻንጣዎች ናቸው ይላል

ስለዚህ ሰው ገድያለሁ ብዙ ገንዘብ አለ እያለ ነው።

አዎ።

ታዲያ ይህማ ወንጀል ነው?

ልክ ነው ሰውየው ሞቷል፣ ገንዘቡ ግን አለ!

ምን ማለትህ ነው?

ሰውየው አንዴ ሞቷል፣ አይነሳም።

የሰውየው መነሳት አለመነሳት ሳይሆን፣ ሰው ተገድሏል።

አዎ ተገድሏል። ገንዘቡ ግን አልሞተም።

የተዘረፈው ገንዘብ ለመንግሥት መመለስ የለበትም?

እንመልሰው እንዴ? እንዲያውም እንደሱ እናድርግ?

አያይ አሁንማ አንዴ ገብተንበታል።

ከዚህ ነገር በሰላም የሚያወጣን ገንዘቡ ብቻ ነው።

የሰይጣን ጆሮ አይስማውና ገንዘቡ ባይኖርስ?

ምን ይደረጋል? መቅለጥ ነዋ!

ውርደቱ ታየኝ!

ድህነት ላይ ውርደት ብዙ አያስፈራኝም።

እኔምለው ድፍረቱን ከየት አመጣኸው?

እኔ እንጃ ለገንዘቡ ጓጉቼ ሳይሆን በምሬት ተገፍቼ ይመስለኛል።

እሱስ ልክነህ እናትህ ሆድ ብሷቸዋል አሉ።

ማን ነገረሽ?

የምትኩን ሚስት ቅድም ገበያ አገኘኋት?

አዎ ወንድማችን ከሞተ በኋላ ጤና የላትም።

አሁን ትንሽ ደህና ናቸው ግን አንተን ናፍቀዋል አለችኝ።

እኔ መሄድ አልችል። እንዳላመጣት ደግሞ የማይሆን ነው።

ፍቃድ አይሰጡህም?

ቢሰጡኝስ፤ እያወቅሽ በምኔ እሄዳለሁ?

ምናልባት ይሄ የተባለው ገንዘብ እንግዲህ?

ህልም ነው ባክሽ፣ ህልም ነው የሚመስለኝ።

ወይ ጉድ፣ የዘንድሮ ህልም ደግሞ ሳይተኛ ነው።

ሰውየውን ስታዪው ምን አሰብሽ፣ የሚታመን ነው?

ተራ ሰው አይመስልም፣የሚያደርገውን ያውቃል።

ሌባ የሚባልም ሰው አይደለም።

በፍጹም

እኔም እንደሱ ነው የተሰማኝ። የተማረም ይመስላል።

ትምህርቱን እንኳ ተወው፣ ለኛ ምን ያደርግልናል?

እንዴት?

የተማረ ሰው ሁሌም ይጫወትብናል።

ይህም እየተጫወተብን ይመስልሻል?

በእሳት እየተጫወተ? አይመስለኝም።

እሱስ ልክ ነሽ፣ የተማረ ሰው ፈሪ ነው።

ሲደፍሩም እኮ ዓይን አውጣ ናቸው።

ከመግደል አይመለሱም።

ይህኛውም ተናገረ እኮ፣ ሰው ገድያለሁ አለ።

‘የተማረ ይግደለኝ’ መሆኑ ነው።

ግን ደግሞ እኔንም ፈርቷል?

ለምን?

ገንዘቡን ካገኛችሁ በኋላ ትገድሉኛላችሁ ይላል።

እንበልና ገንዘቡ ቢገኝ ሰውየውን ምን ታደርገዋለህ?

አልገድለውም መቸም።

ባይገኝስ?

አንቺ ሰው አሁንስ እሱን መሰልሽኝ

አንተም እሱን እየመሰልከኝ ነው። ተቀይረሃል።

የገንዘብ ነገር ያመሳስላል ልበል።

ተማክረው ያደረጉት ነገር ጥሩ ነው።

እሱ ግን ምን የሚፈልግ ይመስልሃል?

መታሰርም፣ አልመታሰርም፣ ገንዘብም አይፈልግም።

መያዜ እንደሁ አይቀርም ብሎ ይሆን?

ፖሊሶች ሊገድሉኝ ይችላሉ ብሎ ፈርቶም ሊሆን ይችላል።

ታዲያ ካንተ ጋር ለምን ወጣ?

እኔም የገረመኝ እሱ ነው።

በል እስኪ ሂድና በሩን አንኳኳ አልወጣ አለ እኮ።

ቢወጣስ ምን እንለዋለን?

እሱስ ቢወጣ ምን ሊለን ይችላል?

ገንዘቡ ቦታ ልውሰዳችሁ ቢለንም የምናደርገውን ማሰብ አለብን።

እሱም አለ ለካ! ቢገኝስ በምን እና እንዴት እናመጣዋለን?

ገንዘቡማ ከተገኘ እንኳን ገንዘቡ እኛም እዚህ አንመጣም።

ቀልደኛ ነሽ!

እውነቴን ነው ለምን እንመጣለን?

የት እንሄዳለን?

እንጠፋለና?

ወዴት?

ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ ይላሉ።

እውነትሽን ነው፣ ስንቱን እያየን ነው።

አዎ እንዲያውም አንጠፋም እንታያለን።

ልክ ነሽ ገንዘብ አይደብቅም፣ አደባባይ ያውላል።

አሁን ቢሆንስ ሌሊት ነው ጧት ነው የምንሄደው?

የት?

ገንዘቡ ቦታ ነዋ?

ጧት ላይ ነው እንጂ ሌሊትማ አደጋ ነው።

ምን አደጋ አለው?

ፖሊሶቹ ጓደኞችህ ቢያዩ ብዬ ነዋ?

የምንሄደው በመኪና ነው በምን ያዩናል?

መኪና ከየት እናመጣለን?

መኪናማ ማግኘት አለብን ያንን ሁሉ ገንዘብ በምን እንጭናለን?

ይሄ ነገር ጣጣው በዛ!

ገንዘብ እኮ ነው ጣጣው አያልቅም።

ገና ሳናገኘው ሆነ እንጂ ባልከፋ።

መጫን ማውረድም አለ።

አዎ ገንዘብ ሲበዛ እኮ ሸክም ነው ይከብዳል።

በመጀመሪያ በአማርኛ በለደስታ የታተመ። በደረጀ ደስታ።

Subscribe to Ledesta

New writing in your inbox. English and Amharic.

Support Ledesta

Or contribute directly to sustain the publication.

Donate
አጋራ
Scroll to Top